አላህ ሚስቶችን ረስቷቸዋልን?

 

 

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

 

 

 

‹እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን በነሱ እናስጠጋለን ከሥራቸውም ምንንም አናጎድልባቸውም ሰው ሁሉ በሠራው ሥራ ተያዢ ነው፡፡› ቁርአን 52.21፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ያሉትን ‹ዝርያቸውም› እና ‹ዝርያቸውን› የሚሉትን ቃላት የተለያዩ የቁርአን የእንግሊዝኛ ትርጉሞች እንደሚከተለው አስቀምጠዋቸዋል፡፡ በፒክታል ትርጉም ከአማርኛው ጋር ተመሳሳይ የሆኑት ‹ዝርያዎች› እና ‹ዝርያቸውም›፤ በዩሱፍ አሊ ትርጉም ‹ቤተሰባቸውም› እና ‹ቤተሰቦቻቸውን› በሚሉት ሲተረጎሙ፣ በሻኪር ትርጉም ደግሞ ‹ልጆቻቸውም› እና ‹ልጆቻቸውን› በሚሉት ቃላት ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የትኛው ነው ትክክለኛው ትርጉም? በእርግጥ ‹ቤተሰቦች› የሚለው የዩሱፍ አሊ ትርጉም ‹ልጆች› ከሚለው ከሻኪር ትርጉም ሰፋ ያለ ሐሳብን የያዘ ቃል ነው፡፡ ‹ቤተሰብ› ሚስትንም ይጨምራል (ወይንም ምናልባትም በእስልምና ‹ሚስቶችን› የብዙ ቁጥር)፤ እንዲሁም ወላጆችንም እንኳን ሳይቀር ይጨምራል፡፡ ይሁን እንጂ ዩሱፍ አሊ በትርጉሙ ውስጥ ‹ቤተሰቦች› የሚለውን ቃል ለምን ተጠቀመበት? ይህ ትንሽ የሚባል ስህተት ብቻ ነውን? ያልታሰበበት ግዴለሽነት ነውን? ወይንስ እሱ እንደገና በተሳሳተ ትርጉሙ ውስጥ ጥልቅ የሆነ ችግርን ለመሸፈን መሞከሩ ነውን? እየሆነ ያለውን በትክክል ለመረዳት ይህንን ቁጥር በአውዱ ውስጥ ማንበብ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህም ቁርአን 52.17-21 እንደሚከተለው ይላል፡-

‹አላህን ፈሪዎቹ በእርግጥ በገነቶችና በጸጋ ውስጥ ናቸው (ቁጥር 17)፡፡ ጌታቸውም በሰጣቸው ፀጋ ተደሳቾች ኾነው (በገነት ውስጥ ናቸው)፡፡ የገሃነምንም ስቃይ ጌታቸው ጠበቃቸው (ቁጥር 18)፡፡ ትሠሩት በነበራችሁት ምክንያት ተሰደሳቾች ኾናችሁ ብሉ ጠጡም (ይባላሉ) (ቁጥር 19)፡፡ በተደረደሩ አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ኾነው (በገነት ይኖራሉ)፡፡ ዓይናማዎች በኾኑ ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን (ቁጥር 20)፡፡ እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን በነሱ እናስጠጋለን ከሥራቸውም ምንንም አናጎድልባቸውም ሰው ሁሉ በሠራው ሥራ ተያዢ ነው (ቁጥር 21)፡፡›

በአውዱ መሰረት ልጆች (ዝርያዎች) የሚኖሩ ከሆነ እናቶችም ለመኖራቸው በጣም ግልጥ መሆን አለበት፡፡ ልጆች የወንዶች ትምክህትና በሕይወት ውስጥ ያፈሯቸው መሆናቸው ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ልጆቻቸው ከእነሱ ጋር በገነት መሆናቸው ለእነሱ (ለወንዶቹ) ትልቅ መፅናናት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አባቶቻቸው ከሚያደርጉት በላይ እናቶች ልጆቻቸውን ይወዳሉ፡፡ እነሱንም በማሳደግ ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ ወንዶቹ ውጪ ሲውሉ፣ አንድ ዓይነት ሙያ ሲኖራቸው፣ ገንዘብን ወደቤት ሲያመጡ፣ በዓለም ውስጥ ስኬት ሲኖራቸው፣ እንዲሁም ብዙውን ታዋቂነት ሲያገኙ፣ ሴቶቹ በቤት ይቆያሉ እናም እራሳቸውን በልጆቻቸው ላይ ያውላሉ (ማለትም ለልጆቻቸው ከፍተኛ መስዋዕትነትን ይከፍላሉ)፡፡ ለሴቶች ብዙውንም ጊዜ የሚኖራቸው ነገር ልጆቻቸው ብቻ ናቸው፡፡ እናም እዚህ አሁን በዚህ የቁርአን ክፍል የሚነገራቸው ነገር፤ በሚመጣው ሕይወት ልጆቻችሁ ከአባቶቻቸው ጋር ይሆናሉ ተብሎ ነው፡፡ እነሱም ሌሎችንም ሴቶች ጨምሮ ወንዶቹ ከሚያገኙት መካፈል ቀርቶ ልትጠቀሱም እንኳን የምትበቁ አይደላችሁም እየተባሉ ነው፡፡

ስለዚህም በትክክል እኛ እዚህ ላይ እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሰዎች ሚስቶች የት ናቸው? (መጨረሻቸውስ ምንድነው?) በማለት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በቁጥር 20 ላይ ለአማኞቹ (ወደ ገነት ሲገቡ) ‹ዓይናማዎች የኾኑ ነጫጭ ሴቶች› ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ማለትም የምድራዊ ሚስቶቻቸውን ሳይሆን ነገር ግን ውብ ሴቶች በተለይም ለእነዚህ ታማኞች ለተባሉት የግብረ ስጋ እርካታ ሰጪዎች እንዲሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ልጆቻቸውን እንደገና እንደሚያዩአቸውም ቃል ተገብቶላቸዋል (ይህም በመሐመድም ካመኑ ጭምር ነው)፡፡

አማኞቹ (ማለትም ወንዶቹ) ፍፁም፣ ውብ፣ እና ስሜታዊ ሴቶች ይሰጧቸዋል፡፡ ስለዚህም ስለ አሮጊቶቹ፣ ጨቅጫቃዎቹ፣ አስቀያሚ እና በምድርም አብረው ለመኖር አስቸጋሪ ስለነበሩት ሚስቶቻቸው ስለምን ይጨነቃሉ? በእርግጥም የእስላማዊው ገነት የወንዶች ዓለም ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ቁርአን የመጣውና የተቀናበረው፤ በዙሪያው ያሉ የሌሎችን ሰዎች ታማኝነት ለማግኘት ከሚጥር አንድ ሰው ቅዠትና ግምት ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ ይህንንም ጥረቱን (መጣልኝ በሚለው) በመገለጡ ከሚሰጣቸው የተስፋ ቃል ኪዳኖች ውስጥ በመጨመር ነው፡፡ ስለዚህም ቁርአን (በምንም ዓይነት መንገድ) የእግዚአብሔር ቃል አይደለም፡፡

ይህ የቁርአን 52.21 ቃልና አብሮት ያለው አውድ ፍትሐዊ ያልሆነና ለሴቶች እጅግ በጣም ጨካኝ የሆነ ክፍል ነው፡፡ በተመሳሳይም መንገድ ዩፉፍ አሊ ቢያንስ፣ ቢያንስ በዚህ ጥቅስ በጣም አፍሯል፡፡ የቁርአን 52.21 የተሳሳተው የእሱ ትርጉም የሚያሳየው እሱ ምን ያህል በዚህ ደስተኛ እንዳልሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ጥቅሱ በምዕራባውያን አንባቢዎች በኩል ተቀባይነትን እንዲያገኝ ለማድረግ ዩሱፍ አሊ ከፍተኛ ጥረትን እንዳደረገ ነው፡፡

ማስታዎሻ፡- የማታምን እና አስቸጋሪ ባህርይ ያላት ሚስት ላለው ለአንድ የተወሰነ ታማኝ አማኝ እንደዚህ ዓይነት ‹መገለጥ› ቢሰጥ ኖሮ ምናልባትም ይህ ተቀባይነት ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ጥቅስ ሐሳብ አጠቃላይ ነው፣ ቃል ኪዳኑም የተሰጠው ለሙስሊም አማኞች ሁሉ በሙሉ ነው፡፡ ይህም የሚጨምረው ሚስቶቻቸው አማኞች እና ታማኞች የሆኑትን ሙስሊሞች ጭምርም ነው፡፡

እግዚአብሔር እውነተኛና ፍትሐዊ ነው በማለት የሚያምን ማንም ሰው ቢኖር ቁርአንን በምንም መንገድ መቀበል የለበትም፡፡ ቁርአን የእግዚአብሔር ቃል አይደለምና፡፡

ለሙስሊም ሴቶች በሙሉ፤ ሊታሰብበት የሚገባ ጥያቄ፡- ‹ሙስሊም ሴቶች እናንተ በገነት ውስጥ የምታገኙት ምንድነው?›

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

የሙስሊሞች ቁርአን እና የእስልምና ትምህርት በሴቶችና በወንዶች መካከል ከፍተኛ ልዩነትን እንደሚያደርግ እጅግ በጣም ብዙ ማስረጃዎች መካከል ቁርአን 52.21 አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የቀረበው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው ቁርአን 52.17-21 ሲታሰስ፣ ሚስቶችን ማለትም አጠቃላይ በሆነ መልኩ ሴቶችን አላህ እረስቷቸዋል፣ ወይንም አላህ ሴቶችን ከወንዶች የተለየ አድርጎ ያያቸዋል፣ ወይንም አላህ በመንግስቱ ለሴቶች ቦታ የለውም ማለት ነው ወደሚል ድምዳሜ ያመጣናል፡፡

ከእነዚህ ከሦስቱ አንዱም እንኳን እውነት ቢሆን አምላክ ፍትሐዊ አይደለም ማለት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ወንዶቹ አማኞች በገነት ውስጥ ዓይናማዎች የሆኑ ሴቶች ሲሰጣቸው ሴቶቹ አማኞች ግን ስለሚያገኙት ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡ ይህም ሌላው አምላክን ፍትሐዊነቱን በግልጥ እንዳላስቀመጠ የሚጠቁም ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለሴቶችና ስለወንዶች አማኞች የሚናገረው ምንድነው? ሴቶች አማኞች ከወንዶች አማኞች በተለየ መንገድ ነው ወይ የሚታዩት? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ የምናገኘው መልስ በጣም ግልጥ ነው፡፡ ወንዶችም ሴቶችም ኃጢአተኞች ከመሆናቸው የተነሳ ሁለቱም ንስሐ ገብተው ወደ አዳኙ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቢመጡ እኩል የዘላለምን ሕይወት እንደሚወርሱ ነው፡፡

በመንግስተ ሰማይም ወይንም በገነት ውስጥ ለወንዶች ልዩ እንክብካቤ እንደሚደረግ፣ ሴቶች ደግሞ የወንዶች ደስታ ሰጪዎች ሆነው አልቀረቡም፡፡ በ1 ጴጥሮስ 3.7 ላይ እንደተገለፀው አማኞቹ ሴቶች ከወንዶች ጋር አብረው የሕይወትን ፀጋ ወራሾች መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህም ወንዶች በዚህ ዓለም ላይ እያሉ ከሚስቶቻቸው ጋር እግዚአብሔር እንደሚፈቅደው መልካም ኑሮን አብረዋቸው እንዲኖሩ፣ ሚስቶቻቸውንም እንዲያከብሩዋቸውም ያዛል፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ለሙስሊም ወንዶችም ሆነ ሴቶች የሚያቀርቡት ጥሪ በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጠው መሠረት ንስሐ እንዲገቡና የዘላለምን መንግስት ሕይወት በእግዚአብሔር ፀጋ መሠረት በማግኘት መዳናቸው እርግጠኛ እንዲሆን በጌታ በኢየሱስ በአዳኙ እንዲታመኑ ነው፡፡ ለዚህ ሊረዳችሁ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ነውና መጽሐፍ ቅዱስን እንድታገኙ እና እንድታነቡ የዘላለም ሕይወት መልክእቱንም እንድትታዘዙ በእግዚአብሔር ፍቅር እንጋብዛችኋለን ጌታ ይርዳችሁ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: Did Allah forget the wives?

እስልምና መልስ አማርኛ  ናው ገጽ