እስልምና እና ሽብርተኝነት
ማርክ ኤ. ገብርኤል
ቅንብር በአዘጋጁ

 

መግቢያ

 

በዚህ መጽሐፍ የሽፋን ገፅ ላይ የምትመለከቱት ሥም በግብፅ ሳለሁኝ በቤተ ሰቦቼ የተሰጠኝ ሥም አይደለም፡፡ ነገር ግን ራሴን ለመጥቀም በማሰብ ክርስቲያኖችንም ሆነ ሙስሊሞችን ወይንም ደግሞ ሌሎች ሰዎችን በሥሜ የማታለል ፍላጎት እንደሌለኝ ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡  ይልቁኑ ሥሜን መቀየር የመረጥኩት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡

 

ምክንያት 1

 

ግብፅን ከለቀቅሁኝ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት እዚያ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ተደረግሁኝ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሙስሊሞችን ማገልገል ስጀምር በሙስሊሙ ስሜ በጣም ታዋቂ ሆንኩኝ፡፡ ለአራት ዓመታት ያህልም አክራሪ ሙስሊሞች ክትትል ሲያደርጉብኝ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ ራሴን መሸሸግ ነበረብኝ፤ በየወሩም ደግሞ ከከተማ ወደ ከተማ የመኖርያ ቤቴን ማዛወር ነበረብኝ፡፡ በደቡብ አፍሪካ በነበርኩበት ጊዜ የመጀመርያ መጽሐፌን ስጽፍ ሥሜን ማስፈር ይኖርብኝ እንደሆን ከመጋቢዬ ጋር ተመካከርን፡፡ ለደህንነቴ ሲባል ሥሜ እንዲቀየርም ወሰንን፡፡

 

ምክንያት 2

 

ክርስትናዬን በሙስሊም ሥም መኖር ምቾት አልሰጠኝም ነበር፡፡ የሙስሊም ሥሜ የአሮጌው ማንነቴ አካል መስሎ ተሰምቶኝ ነበር፡፡ አንድ ሰው በዚያ ሥም ሲጠራኝ የአሮጌውን ኑሮዬ ትውስታ ይመጣብኛል፡፡ በክርስቲያን ሥም መኖር እፈልጋለሁ፡፡

 

የሥሜ ምርጫ

 

ማርክ (ማርቆስ) የሚለውን የመጀመርያ ሥም አድርጌ የመረጥኩበት ምክንያት ማርቆስ የወንጌል ጸሐፊ ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም ማርቆስ የምስራቹን ወደ ግብፅ ይዞ የሄደ የመጀመርያው ክርስቲያን ነበር፡፡ ኢየሱስ ሰባዎቹን ከኢየሩሳሌም በሰደደ ጊዜ ማርቆስ በግብፅ ወደምትገኘው የእስክንድርያ ከተማ ወንጌልን ይዞ መጥቶ ነበር፡፡

 

ገብርኤል የሚለውን የመጨረሻ ሥም የመረጥኩበት ምክንያት ደግሞ ገብርኤል የመሲሁን መምጣት የምስራች ለድንግል ማርያም ይዞላት የመጣ መልአክ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ እንደዚሁም ይህ መጀመርያ በደቡብ አፍሪካ ያገኘሁት እና ወደ ቤተ ክርስቲያን የጋበዘኝ ክርስቲያን ሥም ነው፡፡

 

 

 

የቁርአን ጥቅሶች

 

የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁርአን ሱራዎች በመባል በሚታወቁ 114 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው፡፡ ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሱራዎቹም በቁጥሮች የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ የቁርአን ኮፒ ካላችሁ ሱራዎችን እና ቁጥሮችን በመጠቀም ምንባቦችን አውጥታችሁ መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ሙስሊሞች ብዙ ጊዜ ምዕራፎችን የሚጠሩት ሥያሜዎቻቸውን በመጠቀም ነው ነገር ግን ይህ ለምዕራባውያን አንባቢዎች እምብዛም ጠቃሚ ስላልሆነ ከያንዳንዱ ማጣቀሻ ጋር እነዚህን አልጨመርኩም፡፡

 

ሁለት የተለያዩ የእንግሊዘኛ ቁርአን ትርጉሞችን ተጠቅሜአለሁኝ፡፡ አንደኛው በአብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተተረጎመው ቅጂ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኖብል ቁርአን በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ በሰዑዲ አረብያ ንጉሥ በ1998 ዓ.ም. የታተመ ነው፡፡ ይህ ትርጉም አምፕሊፋይድ ባይብል በመባል ከሚታወቀው የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ጋር ይመሳሰላል ምክንያቱም በቅንፍ ውስጥ በተደረጉ ሐተታዎች የምንባቡን ትርጉም ያብራራልና፡፡ [በዚህ የአማርኛ ትርጉም ውስጥ የተጠቀምነው በ1962 ዓ.ም. የተተረጎመውን እና በነጃሺ ኣሳታሚ ድርጅት የታተመውን የቅዱስ ቁርአን የአማርኛ ትርጉም ሲሆን ጸሐፊው ከተጠቀመው ኖብል ቁርአን የእንግሊዘኛ ትርጉም ጋር ይቀራረባል፡፡]

 

ነገር ግን ምዕራባውያንን ሊያስበረግጉ የሚችሉ ምንባቦች ሲያጋጥሙ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች የአረብኛውን ትክክለኛ መልዕክት እንደማያስቀምጡ ልታውቁ ይገባል፡፡ [ስለ አማርኛውም ትርጉም ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል፡፡]

 

እያልኩ ያለሁት ነገር በትክክል እንዲገባችሁ የሚረዳችሁ ምሳሌ እነሆ፡፡ ሱራ 8፡39 ቁርአንን የማይቀበሉ ሰዎችን በተመለከተ በጣም ቁልፍ ነው ነገር ግን የሚከተለው ትርጉም አሻሚ ነው፡

 

ምንም  ዓይነት ሁከት ወይንም ጭቆና እስከማይኖር ድረስ ተዋጓቸው፤ እዚያም ፍትህ እና በአላህ ማመን በሙላት እና በሁሉም ቦታዎች ይገኛልና፡፡

 

                                                የአሊ ትርጓሜ

 

የኖብል ቁርአን ትርጉም ደግሞ ትንሽ የተሻለ ቀጥተኛ ነው፡፡

 

ምንም ዓይነት ፊትናህ (አለማመን እና መድብለ አማልክታዊነት፣ ማለትም ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክቶችን ማመን) እስከማይኖር ድረስ ተዋጓቸው፤ ኃይማኖትም (አምልኮም) ለአላህ ብቻ ይሆናል [በመላው ዓለም]፡፡

 

[የአማርኛው ትርጉምም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ነው]

 

ሁከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሏቸው፡፡

 

ይህንን መጽሐፍ ለማንበብ መርጃዎች

 

የእስልምናውን መስራች በተመለከተ “ነቢዩ መሐመድ” በማለት የጠቀስኩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ይህንን የተጠቀምኩበት ምክንያት በእስልምናው ዓለም ከሚገኙ ብዙ መሐመዶች እርሱን ለመለየት ነው፡፡

 

ለምዕራባውያን አንባቢያን የአረብኛ ስሞች እንደሚያስቸግሩ ብዙ ጊዜ ተነግሮኛል፡፡ ስታነቡ ሳላችሁ ሊረዷችሁ የሚችሉ ጥቂት ሐሳቦች እነሆ፡

 

ቢን ወይንም ደግሞ ኢብን የሚለው ቃል “የእገሌ ልጅ” እንደማለት ነው፡፡ አል የሚለው ቃል በእንግሊዘኛ “the” የሚለውን ለማመልከት ነው፡፡

 

ስሞችን እና ሌሎች ቁልፍ ፅንሰ ሐሳቦችን በትክክል መረዳት ትችሉ ዘንድ የቃላት መፍቻን በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ አስቀምጬላችኋለሁ፡፡

 

እንደ ምንጭ የተጠቀምኳቸው ብዙ መጻሕፍት ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ያገኘኋቸው እና በጥቁር ገበያ ላይ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን ሙሉ የሆነ የህትመት መረጃዎችን ለመስጠት ሞክሬአለሁኝ፡፡

 

ወደ ማውጫው መመለሻ

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ