የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አራት ክፍል አራት

ስለ አዳም ስለ ነፍሳት ሚዛንና ወደ ሲዖል ስለመሄድ የቁርአን ሐሳቦች   

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

8. የአዳም አፈጣጠርና በመላእክት መመለኩ

በቁርአን 3.52 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፡- ‹አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው፤› ከዚያም በጥቅሱ ውስጥ ለአዳም፣ ‹ከዐፈር ፈጠርነው ከዚያም ለርሱ (ሰው) ኹን አለው ኾነም›፡፡ (ሰው የሚለው ቃል በአማርኛው ቁርአን ለማብራሪያ የተጨመረ ነው)፡፡

የአዳምን ከአፈር አፈጣጠር በተመለከተ ልማድ የሚነግረን ነገር ታላቁ እግዚአብሔር እርሱን ለመፍጠር በፈለገ ጊዜ እርሱ መላእክትን በየተራ እየላከ በእጃቸው አፈርን (ከመሬት) እንዲያመጡለት አደረገ፡፡ ምድርም ብዙዎቹ የአዳም ዘሮች በገሃነም እሳት እንደሚኮነኑ በማወቅ እነዚህ መልእክተኞች ከእርሷ ላይ ምንም ነገርን (አፈርን) እንዳይወስዱ ለመነቻቸው፡፡ ስለዚህም ሁሉም ከመጨረሻው በቀር ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፤ አዝራኤል ግን የምድርን ልመና እምቢ በማለት በእጁን ሙሉ አፈርን ይዞ ተመለሰ፡፡ አንዳንዶች በመካ የሚገኘው ካኣባ የተገነባው ከዚያ ቦታ (አዝራኤል አፈር ከዘገነበት) ላይ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ከመላው የምድር ፊት ላይ ነው ይላሉ፡፡ እርሱም ወደ እግዚአብሔር አመጣው እንዲህም አለ፡- ‹ኦ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ታውቃለህ እነሆ! አምጥቼዋለሁ›፡፡ አቡ ፊዳ በካሚል ኢብን አቲር ስልጣን ላይ እንደሚከተለው ተናግሯል፡- ‹የእግዚአብሔር ነቢይ አለ፡ ‹በእውነት እግዚአብሔር ታላቁ አዳምን ፈጠረው ከምድር ፊት ሁሉ ላይ ከወሰደው አንድ እጅ አፈር ፈጠረው በእርግጥም እርሱ አዳም ተባለ ምክንያቱም እርሱ የተፈጠረው ከምድር ፊት (አዲም) ተፈጥሯልና›፡፡

ይህ ልማድ በጣም አስገራሚ ነው ምክንያቱም እስላምና ለሐሰት ሃይማኖቶች  ምን ያህል ባለ ዕዳ እንደሆነ ሌላ ማስረጃን ይሰጠናልና፡፡ አጠቃላይ ተረቱም የተወሰደው ከማርሲዮን ትምህርት ነው፡፡ በኢዝኒቅ ውስጥ ከተሰጠው ደብዳቤዎች፣ ከአርመኒያን ስራ ‹የኑፋቄዎችን መቃወም› በሚለው ጽሑፍ ውስጥ ካለው ጥቅሱ እንደምንማረው ከሆነ ሁሉም የተወሰደው ከማርሲዮን ነው፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስለነበረው ስለዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ቁንጮ ስንናገር፣ ኢዝኒቅ የጠቀሰው የሚከተሉት አንቀፆች የእርሱን አንዳንድ የተለዩ አመለካከቶችን እንደያዙ ነው፣ ‹የሕጉ እግዚአብሔር ይህ ዓለም ውብ መሆኑን ባየበት ጊዜ ሰውን ከውስጡ ለመስራት ወሰነ፡፡ ከዚያም ወደ ምድር በመውረድ በቁሱ አካሉ ላይ፣ እንዲህ አለ፡- ‹ከአፈርህ ስጠኝ እኔ ደግሞ ከእራሴ መንፈሴን እሰጣለሁ›፣ ቁስ አካሉም ከአፈሩ በሰጠችው ጊዜ እርሱን (አዳምን) ከዚያም መንፈሱን በውስጡ እፍ አለበት ከዚህም የተነሳ እርሱ አዳም ተብሎ ተጠራ ምክንያቱም የተፈጠረው ከአፈር ነበርና፡፡›  

ይህንን ጥቅስ ለመረዳት ማስታዎስ ያለብን ነገር ማርሲዮን በአብዛኛው ይዞ የነበረው አሮጌውን የፐርሺያንን ጥንድ እምነት እንደነበረ ነው፡፡ እርሱም ሁለት የሆኑ የመጀመሪያ ምክንያቶች (የነገር ሁሉ ጀማሪዎች) አሉ የሚለው እምነት ነበር፡፡ እነዚህም አንደኛው ፍፁም መልካምና ሌላው ደግሞ ፍፁም ክፉ ናቸው፡፡ የዚህ ዝቅተኛው ዓለም ፈጣሪ ወይንም ዴሚዩርጎስ እዚህ የታችኛው አምላክ ተብሎ የተጠራው ሲሆን ለአይሁዳውያን የሙሴን ሕግ የሰጣቸው እርሱ እንደሆነ የተነገረለት ነው፡፡ እርሱም ትክክለኛ ነው፣ ነገር ግን ፍፁም ጥሩ ወይንም ፍፁም ክፉ አይደለም ሆኖም ግን ያለማቋረጥ ከክፉ መርሆ ጋር ያለማቋረጥ በጦርነት ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህም በመሐመዳውያን የአፈታሪክ ላይ እንደቀረበው ሁሉ እርሱ የመላእክት አለቃ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እንደ ማርሲዮን አመለካከት ከሆነ ዴሚዩርጎስ በመጀመሪያ ይኖሩ የነበረው በሁለተኛው ሰማይ ላይ ነበር እንዲሁም ስለ ታላቅ የሆነ የመልካምነት መርሆ አያውቅም ነበር፣ እርሱም ማርሲዮን የማይታወቅ አምላክ ብሎ የጠራውን ማለት ነው፡፡ የማይታወቅ አምላክ ተብሎ የተጠራውን መኖር ሲገነዘብ ዴሚዩርጎስ ለእርሱ ጠላት ሆነው፤ ከዚያም ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳያውቁ ለመከልከል ጥረት ማድረግን ጀመረ ከእርሱ ዞር ብለው አምልኮአቸውን  ለእግዚአብሔር እንዳያደርጉ፡፡ ስለዚህም  የሕግ አምላክን ኃይልና የክፉን መርሆ ለማጥፋት፣ እንዲሁም ሰዎችን እውነተኛውን አምላክ ማወቅ እንዲችሉ እንዲመራቸው ታላቁ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ላከው፡፡ ኢየሱስም በእነዚህ በሁለቱም ስብዕናዎች ተጠቅቶ ነበር ነገር ግን እርሱን ሊጎዱት አልቻሉም ነበር እርሱ ለሰዎች ለመታየት እንዲችል ብቻ የሰው አካል ያለው ይመስል ብቻ ነበር እንጂ እውነተኛ አካል አልነበረውም፡፡ እዚህ ላይም እንደገና የምናገኘው የዶሲቲክ መርሆን ነው እርሱም ምንም እንኳን ከመሐመድ አጠቃላይ ትምህርት ጋር ተቃራኒ ቢሆንም ነገር ግን የክርስቶስን መሰቀል በመሰረቱ ይክድ ነበር፡፡

ስለ ዴሚዩርጎስ ማርሲዮን የተናገረው ነገር በአብዛኛው መሐመዳውያን ስለ አዛዚል ካላቸው ተረት ጋር ይስማማል፡፡ አዛዚል የሁለተኛው ሰማይ ነዋሪ ነበር፤ (እንዲሁም በአንዳንድ ልማዶች መሠረት በሰማያት ውስጥ ሁሉ) ወደ ታች ከመወርወሩና ኢብሊስ ወይንም ሰይጣን የሚለውን ስም ከማግኘቱ በፊት፡፡ ነገር ግን የማርሲዮንም የመሐመድም ቃላት በዚህ ነጥብ ላይ ከዞሮአስተርያን አፈታሪኮች ላይ የተወሰዱ መሆናቸው በጣም ግልጥ (ማስረጃ) ያለው ነገር ነው፡፡ እነዚህንም ለሚከተለው ምዕራፍ ጠብቀን ልናቆያቸው ይገባናል፡፡

በማርሲዮን በተከታዮቹ ለዴሚዩርጎስ የተሰጠውን መጠሪያ መገንዘብ ጠቃሚ ነው ስያሜዎቹም ‹የዓለማት ጌታ›፤ ‹የፍጥረታት ፈጣሪ› እና ‹የዚህ ዓለም ገዢ› የሚሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ለእግዚአብሔር የሚገቡ ስያሜዎች ናቸው እንዲሁም በአይሁዶችም በሙስሊሞችም ለእርሱ መጠሪያነት አገልግለዋል፡፡ ሦስተኛው ግን ከዮሐንስ 14.30 ላይ የተወሰደ ሲሆን እርሱም ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕድለ ቢስ በሆነ ስህተት መሐመዳውያን ይህንን ጥቅስ የተረዱት ለመሐመድ የተነገረ ትንቢት አድርገው ነው ስለዚህም ይህንን ማዕረግ ለነቢያቸው መጠሪያነት አውለውታል፡፡

ከአዳም አፈጣጠር ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ቁርአን በተደጋጋሚ የሚናገረው ነገር እግዚአብሔር መላእክትን እንዲያመልኩት እንዳዘዛቸው ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ካሉት ጥቅሶች መካከል የሚከተሉትን እናነሳለን፡-

ቁርአን 2.34 ‹ለመላእክትም ለአዳም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ) ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ ኢብሊስ (ዲያቢሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ ኮራም ከከሐዲዎቹም ኾነ› ቁርአን 17.61፣ ቁርአን 18.50 እና 20.116 ተመሳሳዩን ቃል ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ አቅርበውታል፡፡

ይህ ሐሳብ ከታልሙድ በፍፁም ሊገኝ አይችልም፣ በእርሱም መላእክት ለአዳም ከመጠን በላይ የሆነ ክብር እንደሰጡት ቢነገረንም፣ በተለይ የተቀመጠው ግን እነርሱ ስህተትን ሰርተው እንደነበረ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ያለምንም ጥርጥር የተወሰደው ከዕብራውያን 1.6 ላይ የተጠቀሰውንና፡- ‹ደግሞም በኵርን ወደዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል› የሚለውን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ነው፡፡ የሚመስለውም መሐመድ በእነዚህ ቃላት በጣም እንደተነካ ስለዚህም እንደተለመደው በተሳሳተ መንገድ ተገንዝቦት ‹በኩርን› የሚለው ቃል ክርስቶስ ማለት ሳይሆን አዳም ነው በማለት ተረድቶታል ከዚያም በተደጋጋሚ የዚህን ተመሳሳይ ቃል በቁርአን ውስጥ አስቀምጦታል፡፡ ይህም ለክርስቶስ ስለተሰጠው አምልኮ እንደ መቃወሚያ ክርክርም ቀርቦ ወይንም ጥቅም ላይ ውሎ ይሆናል ምክንያቱም ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ቁርአን 3.52 ላይ የነገረን ነገር በእግዚአብሔር ፊት ኢየሱስ ልክ እንደ አዳም ያለ ብቻ ነው፤ ምንም ጥርጥር የለውም ልክ እንደ አዳም ያለምንም ሰዋዊ አባት ነው (ልክ አባሲና ጃላላይን እንደገለፁት) ነገር ግን በእነዚያ ጽሑፎች ውስጥ እርሱ መለኮት ተብሎ መጠቀስ አይኖርበትም፡፡

9. ሰዎች ሁሉ ወደ ሲዖል መሄድ አለባቸው

ይህ አስገራሚ ሐሳብ የተገለፀው በቁርአን 19.69-73 ላይ ነው፡፡ ‹ከዚያም ከየጭፍሮቹ ሁሉ ከነርሱ ያንን (እርሱ) በአልረህማን ላይ በድፍረት በጣም ብርቱ የኾነውን እናወጣለን፣ ከዚያም እኛ እነዚያን እነሱ በርሷ ለመግባት ተገቢ የኾኑትን እናውቃለን፡፡ ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም (መውረዱም) ጌታህ የፈረደው ግዴታ ነው፡፡ ከዚያም እነዚያን የተጠነቀቁትን እናድናለን አመጠኞቹንም የተንበረከኩ ኾነው በውስጧ እንተዋቸዋለን፡፡ በነርሱም ላይ አንቀጾቻችን ግልፅ ማስረጃዎች ኾነው በተነበቡ ጊዜ እነዚያ የካዱት ለነዚያ ላመኑት ከሁለቱ ክፍሎች መኖሪያው የሚበልጠውና ሸንጎውም ይበልጥ የሚያምረው ማንኛው ነው ይላሉ›፡፡

ይህ አንቀፅ ለተሰጡ ሙስሊሞች ሁሉ ደስታን በጣም ነስቷቸዋል፣ የገሃነም እሳት አያጠቃንም በማለት ተስፋ ቢያደርጉም እንኳን ደስተኝነት አይሰማቸውም፡፡ የዚህን ጥቅስ ግልፅ ትርጉም ለማውጣት ተንታኞች ሁሉ በቆራጥነት ቢታገሉም (ምንም እንኳን በምንም ዓይነት መንገድ በአመለካከቶቻቸው ላይ በፍፁም ባይስማሙምም) ጥቅሱ የሚለው ግን በቀላሉ ሁሉም ሰው እውነተኛ ሙስሊሞችም እንኳን ወደ ሲዖል እሳት መምጣት እንዳለባቸው ነው፡፡ ሲራት በፍርድ ቀን እንደሚለው ይህንን የሚያደርጉት በድልድዩ ላይ ሲያልፉ ነው፡፡ ይህ አገላለፅ ተቀባይነት ካለው ክፍሉን መመልከት ያለብን በሚቀጥለው ምዕራፍ በምዕራፍ አምስት ውስጥ የዞሮአስተርያንን ተፅዕኖ በእስልምና ምንጭ ላይ ስንመለከት ነው፡፡ ነገር ግን ከጠቀስናቸው ጥቅሶች ቋንቋዎች መሐመድ ፐርጋቶሪ (ማለትም የሙታን ነፍሳት በሲዖል ውስጥ የተወሰኑ ጊዜያት ይቆያሉ የሚል የካቶሊክ አስተምህሮ) ላይ ያለውን እምነቱን መግለጡ ሊሆን የሚችል የመሆኑ እውነታ በጣም ያመዝናል፡፡ ይህ ደግሞ ከሆነ ይህን ተምሮ የነበረው በጊዜው ከነበሩ ከክርስትያኖች መሆን አለበት፡፡ ይህንን ትምህርት ከማርቆስ 9.49 ‹ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል።› እና ከ1ቆሮንቶስ 3.13 ‹የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።› በእርግጥ እነዚህ ጥቅሶች ሲነበቡ መሐመድ ስምቷቸው ሊሆን ይችላል እናም እነርሱን በዚህ በተሳሳተ መንገድ ተረድቷቸዋል፣ ነገር ግን ስህተቶቹን እንዳሉ እንደተሰሩ የወሰዳቸው መሆኑ በጣም አሳማኝ ነው፡፡ ‹የአባርሃም ኪዳን› የሚነግረን የእያንዳንዱ ሰው ስራ በእሳት እንደሚፈተን ነው እሳቱም የእያንዳንዱን ሰው ስራ ካቃጠለው ደግሞ ሰውየው በእሳት ላይ በሚኖረው መልአክ ወደ ስቃይ ቦታ ይወሰዳል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በቁርአን ውስጥ ብቻውን የሚገኝ አንቀፅ ትርጉም ግልፅ አይደለም፣ እኛም ስለ ፐርጋቶሪ ዶክትሪን ምንጭ ከዚህ በላይ መጠየቅ አያስፈልገንም፡፡

10. ሚዛኑ

ስለ ሚዛኑ (በመጨረሻው ቀን መልካም ስራዎችና ክፉዎች ስለሚመዘኑበት)  በቁርአን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጠቀሳ ተደርጓል ከእነዚህም ውስጥ ዋናዎቹ፡- ቁርአን 7.8-9 ‹ትክክለኛውንም ሚዛን የዚያን ቀን ነው ሚዛኖቻቸው የከበዱላቸው ሰዎችም እነዚያ እነርሱ የፈለጉትን ያገኙ ናቸው፡፡ ሚዛኖቻቸው የቀለሉለባቸው ሰዎችም እነዚያ እነርሱ ምራቶቻችንን ይክዱ በነበሩበት ምክንያት ነፍሶቻቸውን ያከሰሩ ናቸው›፡፡ ቁርአን 21.47 ‹በትንሳኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበድልም (ሥራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ›

ቁርአን 42.17 ‹አላህ ያ መጽሐፉን በእውነት ያወረደ ነው ሚዛንንም (እንደዚሁ) ሰዓቲቱ ምናልባት ቅርብ መኾንዋን ምን ያሳውቅሃል?› ቁርአን 101.6-11 ‹ሚዛኖቹ የከበዱለት ሰውማ እርሱ በምትወደድ ኑሮ ውስጥ ይኾናል፡፡ ሚዛኖቹም የቀለሉበት ሰውማ መኖሪያው ሃዊያህ ናት እርሷም ምን እንደ ኾነች ምን አሳወቀህ? (እርሷ) በጣም ተኳስ እሳት ናት፡፡›

በልማድ ስልጣን ላይ ተንታኞች እነዚህን ጥቅሶች ሲገልጧቸው በትንሳዔ ቀን በሰማይና በምድር መካከል እግዚአብሔር ሚዛንን እንደሚገነባና እርሱም ምላስና ሁለት የመመዘኛ ሳህኖች ወይንም መለኪያዎች እንደሚኖሩት ነው፡፡ ይህም በተለየ ሁኔታ የሚጠበቀው የሰዎችን መልካም ስራዎች ከክፉ ስራዎቻቸው ለመመዘን ነው ወይንም እነዚህ የተመዘገቡባቸውን መዝገብ ለማሳየት ነው፡፡ እውነተኛ አማኞች መልካም ስራዎቻቸው ሲቀመጡ ሌላውን እንደሚመዝኑ ይመለከታሉ፣ ክፉ ስራዎቻቸውን የያዘው  የማይምነት መለኪያ መልካም ስራዎቻቸውን የያዘው ክፍል በክፉ ስራዎቻቸው ተመዝኖ ቀልሎ ያዩታል፡፡ ከአማኞች መልካም ስራዎች መካከል አንዲቷም እንኳን አትጣልም፣ እንዲሁም በእርሱ ኃጢአት ላይ ምንም ነገር አይጨመርም፡፡ መልካም ስራዎቻቸው የሚያመዝኑላቸው ገነት ውስጥ ይገባሉ ነገር ግን መልካም ስራዎቻቸው በክፉ ስራዎቻቸው የተመዘኑባቸው እነዚያ ወደ ሲዖል እሳት ውስጥ ይጣላሉ፡፡

የሰዎችን ተግባራት ስለመመዘን ሐሳብ የሚገኘው በታልሙድ ውስጥ እንደሆነ ተጠቁሟል ለምሳሌም ያህል ሮሽ ሃሽሻና ምዕራፍ 17 ይገኛል፡፡ ይህ ምናልባትም የተወሰደው ከዳንኤል 5.17 ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን በዳንኤል ላይ የተነገረው ሚዛን ምሳሌያዊ ነው፣ እንዲሁም የቤልሻዛር መመዘን በትንሳኤ ቀን የሚሆን አይደለም ወይንም ከሞተ በኋላም አይደለም ነገር ግን እርሱ በሕይወት እንዳለ የሚሆን ነበር፡፡ ለዚህ የመሐመዳውያን ፅንሰ ሐሳብ ምንጭ ወደ ሌላ ቦታ መመልከት ይኖርብናል፣ ይህንንም አንድ ጊዜ እንደገና የምናገኘው ‹የአብርሃም ኪዳን› በሚለው በአፖክሪፋል መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ስራ በመጀመሪያ የተጻፈ የሚመስለው በግብፅ ውስጥ ነው፡፡ እርሱም እንደተጀመረ የሚታወቀው ምናልባትም የተቀናበረው በእኛ ዘመን በሁለተኛው ምዕተ ዓመት ወይንም ከሶስተኛው ሳይዘገይ ወደ ክርስትና በተቀየረ አይሁዳዊ ሰው ነው፡፡ እርሱም በሁለት የግሪክ እርምት ጽሑፎች ውስጥ እና እንዲሁም በአረብኛው ትርጉም ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ አንቀፆች በቁርአን ውስጥ ካሉት አንዳንድ ጥቅሶች ጋርና ከኋለኞቹ የመሐመዳን ልማዶች ጋር ያላቸው መመሳሰል በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ዕድል ብቻ (አጋጣሚ ብቻ) ነው ማለት በፍፁም አይቻልም፡፡ የዚህም የሚዛን መጠቀስ በተለይ ‹የአብርሃም ኪዳን› ውስጥ በተለይም ይታያል፡፡

በዚያም ላይ የተጠቀሰው ነገር የሞት መልአክ የአብርሃምን ነፍስ ለመውሰድ በእግዚአብሔር ታዞ በመጣበት ጊዜ ፓትሪያርኩ (አብርሃም) ከመሞቱ በፊት የምድርንና የሰማይን ተዓምራት እንዲመለከት ጥያቄን አቀረበ፡፡ ፈቃድም ተሰጥቶት ወደ ሰማይ አረገ በመልአኩ መሪነት የሚታዩትንም ሁሉንም ነገሮች አየ፡፡ ወደ ሁለተኛውም ሰማይ በደረሰ ጊዜ አንድ መልአክ የሰዎችን ስራዎች የሚመዝንበትን ሚዛን አስተዋለ የሚከተሉት አንቀፆች እንደሚገልጡት፡-

‹በሁለቱ መግቢያዎች መካከል ዙፋን ቆሟል በእርሱም ላይ አስደናቂ ሰው ተቀምጧል በእርሱም ፊት መስተዋት የሚመስል ጠረጴዛ ቆሟል ሁሉም ወርቅ እና በጣም ቀጭን የናይለን ልብስ ለብሷል፡፡ በጠረጴዛውም ላይ ውፍረቱ ስድስተ ክንድ ስፋቱም አስር ክንድ የሆነ መጽሐፍ ተቀምጧል፡፡ በጠረጴዛውም ቀኝና ግራ በኩል ሁለት መላእክት ቆመዋል እነርሱም ወረቀት ቀለምና ብዕርን ይዘዋል፡፡ በጠረጴዘውም ፊት ለፊት ብርሃንን የያዘ መልአክ ተቀምጧል በእጁም ሚዛንን ይዟል በግራም በኩል ደግሞ እሳት መልክ ያለው መልአክ ተቀምጧል፣ ምንም ምህረት የለሽና ኮስታራም ነበር፣ በእጁም ጡሩምባን ይዞ ነበር በእርሱም ሁሉንም የሚበላ እሳት ይዞ ነበር እርሱም የኃጢአተኞች መፈተኛ ነው፡፡ አስደናቂው ሰው በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው እራሱ በነፍሳት ላይ ይፈርድና ይመረምር ነበር፣ በቀኝና በግራ ያሉት ሁለቱ መላእክት ግን ይመዘግቡ ነበር በቀኝ በኩል የነበረው የፅድቅ ስራዎችን ይመዘግብ ነበር በግራ የነበረው ደግሞ ኃጢአቶችን ይመዘግብ ነበር፡፡ በጠረጴዛው ፊት ለፊት ሚዛኑን ይዞ የነበረው ነፍሳትን ይመዝን ነበር እሳትን የያዘው የእሳት መልአክ ደግሞ ነፍሳትን ይፈትን ነበር፡፡ አብርሃምም ዋናውን አዛዥ ሚካኤልን ጠየቀ፡-  ‹እነዚህ የምናያቸው ነገሮች ምንድናቸው?› ዋናውም አዛዥ እንደሚከተለው፡- ‹ቅዱስ አብርሃም የምታየው ነገር ፍርድና ቅጣት ነው› አለው፡፡

ታሪኩም እንደዚያ ይቀጥላል፣ አብርሃምም ያየው መልካምና ክፉ ስራዎቻቸው እኩል የሆኑባቸው እያንዳንዳቸው ነፍሳት ከሚድኑት ወይንም ከሚጠፉት መካከል አልተቆጠሩም ነገር ግን በሁለቱ መካከል ቆመው ነበር፡፡ ይህ የኋለኛው ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ በቁርአን 7.46 ላይ ካለውና ‹በመካከላቸውም ግርዶሽ አልለ (በገነትና በሲዖል) በአዕራፍም ላይ ሁሉንም በምልክታቸው የሚያውቁ ሰዎች አልሉ የገነትንም ሰዎች ሰላም ለናንተ ይኹን በማለት ይጣራሉ እነርሱም (የአዕራፍ ሰዎች) የሚከጅሉ ሲኾኑ ገና አልገቧትም› ከሚለው የመሐመዳውያን እምነት ጋር ይስማማል፣ እንዲሁም በልማድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

መሐመድ በቀጥታ ወይንም በተዘዋዋሪ ስለሚዛን ላስተማረው ትምህርት ከግብፅ ለመጣው ለአፖክሪፋው መጽሐፍ ወይንም ከዚያ በፊት ለነበረውና በዚያን ጊዜ በመጨረሻም በአፍ የተነገረው ሐሳብ ባለዕዳ የነበረ መሆኑን ለመጠራጠር አይቻልም፡፡ እርሱ ከኮፕቲክ ቅምጡ ከማርያም የተማረው ሊሆን ይችላል፡፡ የሰዎችን መልካምና ክፉ ስራዎቻቸውን የመመዘን ፅንሰ ሐሳብ በግብፅ በጣም ጥንታዊ ነገር ነው፡፡ ሐሳቡንም በሙታን መጽሐፍ ‹በፍርድ ትዕይንት› ላይ እናገኘዋለን እነዚህም በጣም ብዙ ግልባጮቻቸው በጥንት የግብፃውያን መቃብሮች ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ ይህንን ስራ በተመለከተ ዶክተር በጅ የተናገረው፡ ‹የሙታን መጽሐፍ በተያያዘ መልኩ ልክ እንደ ግብፃውያን ስልጣኔ ትንጥዊ መሆኑ በትክክል እርግጠኛ ነው ማለትም ምንጮቹ ከታሪክ በፊት የነበሩ ጊዜያት ናቸው ለዚህም ቀናትን መስጠት በፍፁም አይቻልም፡፡ ስለዚህም እኛ በመጀመሪያ የምንነካው ‹ለሙታን መጽሐፍ› ታሪክ የመጀመሪያውን ድንግል መሬት ነው፡፡ ከጥንታዊ መንግስታት ጊዜዎች ልማድ ከተቀበልን በግብፅ ውስጥ ወቅታዊ የነበረውንና 2500 ዓመተ ዓለም ድረስ ወደ ጥንት ሄደን ማየት አለብን፡፡ በዚያም ወቅት አንዳንድ የመጽሐፉ ክፍሎች አሁን ባሉበት ሁኔታ ይገኛሉ እስከ መጀመሪያው መንግስት ግዛት ድረስ፡፡› ጸሐፊውን በተመለከተ እርሱ የተናገረው ነገር፡- ‹በጣም በጥንት ጊዜ  በጣዖቱ ‹ቶት› መለኮታዊ እውቀት በፍጥረት ጊዜ በ‹ታህና ኒሙ› ተግባራዊ የተደረጉትን ቃላት የተናገረው፣ እንዲሁም የአማልክት ጸሐፊ ‹የሙታን መጽሐፍ› ስራ ላይ ተባብረው ነበር፡፡ የዚህ መጽሐፍ ከመሚዎች ጋር መቀበር ዓላማው የሞተው ሰው በሚቀጥለው ዓለም ውስጥ ሊያጋጥመው የሚችለውን አደጋ ሁሉ እንዴት ማስወገድ እንዳለበት እንዲማር ነበር፡፡ ከእርሱም ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ስለሆኑት የግብፃውያን ሃይማኖት ሃሳቦች እንማራለን፡፡ በነፍሳት ላይ የሚሆነውን ፍርድ የሚወክለው ስዕል ምናልባትም ‹የአብርሃም ኪዳን› ላይ እንዳለው የሚሆነው ከሞት በኋላ ወዲያውኑ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም በአጠቃላይ አንድ ዓይነት የሆነ አወቃቀር ቢኖራቸውም በተለያዩ ኮፒዎች ላይ የሚገኘው ዘገባ የተለያየ ነው፡፡ ብዙውንም ጊዜ የሚገኘው ቅርፅ ሁለት አማልክትን ያሳየናል እነርሱም ‹ሆሩስ› እና ‹አኑቢስ› ናቸው፣ እነርሱም የሰውን ልብ በሚዛኑ በአንደኛው መመዘኛ ላይ በመመዘን ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ‹በማት› ምስል ትይዩ ነው፣ ‹ማትም› የእውነትና የብርሃን ሴት አማልክት ናት እርሷም በሌላው (በሁለተኛው) የሚዛኑ መመዘኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ሌላው ጣዖት ‹ቶት› በግብፃውያኑ ‹ተሁቲ› ላይ የሞቱ ሰዎችን ድርጊቶች በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ ይጽፋል፡፡ በሚዛኑም ላይ የተጻፈው ‹የኦሲሪስ ሕይወት ትክክል ሆኗል (ፀድቋል) የሚል ሲሆን በእርሱም ቦታ ላይ ሚዛኑ ‹በሆል› የመለኮታዊ ፍርድ መካከል ላይ ትክክል ሆኗል፡፡ እርሱም አለ፡- ‹ልቡን በተመለከተ ልቡ በቦታው ላይ በኦሲሪስ እንደዚህና እንደዚያ የፀደቀው፡፡› ቶት! በታላቁ ከተማ በህስርት፣ የከተማው ጌታ ሄርሞፖሊስ የቶት ቃላቶች ጌታ ይህንን ይበል፡ ‹የኦሲሪስ ስም በሞተው ሰው ላይ መጠራት እንዲሁም የእርሱ ስም (ለእርሱ ስም መጠራት ክፍት ቦታ በተተወበት ላይ) የሚያመለክተው በፍርድ ፃድቅ በመሆን እርሱ ከኦሲሪስ አማልክት ጋር፣ ከጥንታዊ ግብፆች ታላቁ መለኮት ጋር አንድ ሆኗል፣ ስለዚህም ከክፉ ኃይላት ጥቃት ጥበቃ አለው፡፡ በመለኮታዊው ጸሐፊ ‹ቶት› ምስል ፊት ለፊት አስፈሪ እንሰሳ ቆሟል አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ሴት ውሻ፡፡ ይህም የተገመተው ኃጢአተኞችን ለመዋጥ ነው፡፡ በራሱም ላይ የሚከተለው ነገር ተጽፏል፤ ‹ጠላቶችን በመዋጥ ድል የሚያደርግ የገሃነም እመቤት፣ የገሃም አዳኝ›፡፡ ከእዚህ እንሰሳ ቀረብ ብሎም ሙሉ የሚሰው ነገሮችን ይዞ መሰዊያ ቆሟል ይህም በመግቢያው ላይ ተቀምጦ ለውስጣዊው ቅርፅ ቅርብ ቦታ ላይ ነው፡፡ በቅርፁ ውስጥ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው እራሱ ኦሲሪስ ነው ‹መልካሙ ስብዕና› እርሱም በአንድ እጁ የመንግስት ዘንግ (በትረ መንግስት) በሌላው ደግሞ ጅራፍን ይዟል፡፡ እርሱም እንደ ፈራጅ ተቀምጦ የሞተን ሰው መንፈስ ጉዳይ ለማየት ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም ‹ቶት› የልቡን ሚዛኑን ውጤት በተመለከተ በጥቅልል መጽሐፉ ላይ በሚጽፈው መሰረት ነው፡፡ በኦሲሪስ ፊት ለፊት አንዳንዶቹ የእሱ የማዕረግ መጠሪያዎች ተቀርፀዋል፡፡ እርሱም እንዲህ ይነበብ ይሆናል፡- ‹ኦሲሪስ መልካሙ አምላክ የሕይወት ጌታ ታላቁ እግዚአብሔር የአብት ከተማ ጌታ ያለፉት ዘላለሞች ንጉስ አምላክ›፡፡ ከእርሱም ዙፋን ስር ‹ሕይወትና ጤና› የሚሉት ቃላት በጣም ብዙ ጊዜ ተጽፈዋል፡፡

ከዚህ ስዕል ንፅፅር፣ ‹የአብርሃም ኪዳን› ውስጥና በቁርአን ካነበብነው እርግጥ የሆነው ነገር፣ በቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው ሚዛን እንዲሁም በመሐመድ ልማድ ውስጥ ያለው የሚዛኑ ሐሳብ በመሰረቱ የተወሰዱት ከጥንታዊ የግብፃውያን የጥንት እምነት ተረቶች ላይ ነው፡፡ ይህም የሆነው በኮፕቲክ ክርስትያኗ ሐሳብ አማካኝነት ነው ከ‹አብርሃም ኪዳን› ውስጥ የተጠቀሱት በመጀመሪያ ከተገኙበት አገር በግብፅ ውስጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ሲተላለፉ ቆይተው ነው፡፡

11. በሰማይ የአዳም ሐዘንና ደስታ

በቁርአን 17.1 ላይ የምናነበው መሐመድ ወደ ሰማይ ያደረገውን ጉዞ አፈታሪክ ነው፣ ይህም በመሐመዳውያን ልማድ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ ቦታን ይዟል፡፡ የዚህም ጥቅስ ቃሎች እንደሚከተለው ናቸው፡- ‹ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቅ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኬደው (ጌታ) ጥራት ይገባው ከታምራቶቻችን ልናሳየው (አስኬድነው) እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡)

የዚህን የመሐመድን ወደሰማይ ጉዞ ‹ሚራጅ› ተብሎ የሚጠራውን በተመለከተ በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ ሰፋ ባለ ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ እዚህ ላይ ግን እርሱን የምንመለከተው በዚያ በጣም ዝነኛ ጉዞ ውስጥ ያለውን የመሐመድን አንዱን ክፍል ልምምድ የሚጠቅሰውን ልማድን ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በሚሽካቱል ማሳቢ የተነገረን ነገር እርሱ በሰባተኛው ሰማዮች በታችኛው ውስጥ ሲገባ ስለነበረው ክስተት ነው፡፡

‹ከዚያም እርሱ ታችኛውን ሰማይ ሲከፍትልን እነሆ ሰው ተቀምጦ ነበር፡ በእርሱም ቀኝ እጅ በኩል ጥቁር ምስሎች እና በግራው እጁ በኩልም ጥቁር ምስሎች ነበሩ፡፡ ወደ ቀኙም በኩል ሲመለከት ሳቀ ወደ ግራው ሲመለከት ደግሞ አለቀሰ ... እኔም ለገብርኤል እንዲህ አልኩኝ፡- ‹ይህ ማነው? እርሱም ‹ይህ አዳም ነው እነዚህም ጥቁር ምስሎች በቀኙ በኩልና በግራው በኩል ያሉት የልጆቹ ነፍሶች ናቸው፣ በቀኙ በኩል ያሉት የገነት ሕዝቦች ሲሆኑ በግራው በኩል ያሉት ምስሎች ደግሞ የእሳት ልጆች ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም እርሱ ወደ ቀኙ ሲመለከት ሳቀ ወደ ግራው ደግሞ ሲመለከት አለቀሰ› አለኝ፡፡

ይህም ልማድ የሚከተለው ጥቅስ እንደሚያረጋግጠው በአፖክሪፋዊው ‹የአብርሃም ኪዳን› ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡-

‹ሚካኤል ሰረገላውን አዙሮ አብርሃምን አሳፍሮ ወደ ምስራቅ ሄደ ወደ ገነት የመጀመሪያ በር፡፡ አብርሃምም አንዱ ጠባብና ቀጭን ሌላው መንገድ ደግሞ ሰፊና ትልቅ መንገዶችን አየ፡፡ እዚያም እርሱ ሁለት መግቢያዎችን (በሮችን) አየ፣ አንዱ በር ሰፊ ከሰፊው መንገድ ጋር የሚሄድ ሌላው ደግሞ ጠባብ ከጠባቡ መንገድ ጋር የሚሄዱ ናቸው፡፡ ‹በእነዚያም በሁለቱ በሮች በስተውጪ እዚያ በዚፋኑ ላይ የተቀመጠ ሰውን አየሁ በወርቅ በተሸፈነ ዙፋን ላይ የተቀመጠ ሰውን አየሁ፡ የዚያም ሰው ሁኔታ ልክ እንደ ጌታ በጣም የሚያስፈራ ነበር፡፡ ከዚያም እጅግ በጣም ብዙ ነፍሶችን በመላእክት ሲነዱ እና በሰፊው በር ውስጥ ሲመሩ ተመለከትሁ ከዚያም ሌሎች ጥቂት ነፍሶችን ደግሞ አየሁኝ እነርሱንም መላእክት ተሸክመዋቸው በጠባቡ በር ውስጥ ተወሰዱ፡፡ ያ በወርቃማው ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው አስደናቂው ሰው ጥቂቶች በጠባቡ በር ሲገቡና ብዙዎች ደግሞ በሰፊው በር ሲገቡ ባየ ጊዜ፣ ወዲያውኑ የእራሱን ጠጉርና የፂሙን ፀጉር ያዘና ከዙፋኑ ላይ እራሱን ወደ ምድር ወረወረ ከዚያም አለቀሰና በጣም አዘነ፡፡ ከዚያም ብዙዎች በጠባቡ መንገድ ሲገቡ ባየ ጊዜ ተነስቶ ከመሬት እራሱን በዙፋኑ ላይ አስቀምጦ በታላቅ ደስታ ደስ በመሰኘት ሐሴት አደረገ፡፡ አብርሃምም የመላእክቱን አለቃ ሚካኤልን ጠየቀው፡- ‹ጌታዬ ሆይ የመላእከት አለቃ ይህ በእንደዚህ ዓይነት ክብር ያጌጠው እና ሁሉመናው አስደናቂ የሆነው ሰው ማነው? በአንድ ወቅት ያዝንና ያለቅስ የነበረው በሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ተደስቶ ሐሴት ያደረገው ማነው?› አካል የሌለውም አለው፡ ‹በእንደዚህ ዓይነት ክብር ውስጥ ያለው በመጀመሪያ የተፈጠረው ሰው ይህ አዳም ነው፣ እርሱም አለምን ይዟል ምክንያቱም ሁሉም የተወለዱት ከእርሱ ነውና እርሱም ብዙዎችን በጠባቡ መንገድ ሲገቡ ባየበት ጊዜ ተነስቶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ በታላቅ ሐሴት ደስ እየተሰኘ ምክንያቱም ይህ ጠባብ መንገድ ለፃድቃን ነውና ወደ ሕይወት የሚወስድ መንገድ ነውና በእርሱም ውስጥ የሚገቡት ወደ ገነት ይሄዳሉና በዚህም መሰረት  የመጀመሪያው ፍጥረት አዳም ሐሴትን ያደርጋል ምክንያቱም ነፍሶች ሲድኑ አይቷልና፡፡ ብዙ ሰዎች በሰፊው መንገድ ውስጥ ሲገቡ ሲያይ ከዚያም እርሱ የራሱን ፀጉር ነጭቶ እራሱን ወደ ምድር ላይ ይጥላል በመረረ ሁኔታ በማንባትና በማዘን፡፡ ምክንያቱም ሰፊው በር የኃጢአተኞች ነው ወደ ጥፋት እንዲሁም ወደ ዘላለም ፍርድ ይመራቸዋል፡፡›

12. ከአዲስ ኪዳን ላይ የተወሰዱ

መሐመድ  ከአፖክሪፋዊ ምንጮች ላይ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ነገሮችን ወስዷል፣ ከራሱ ከአዲስ ኪዳን ላይስ ምንም ነገርን አልተዋሰም ወይ? በማለት በመጨረሻ ሊጠየቅ ይቻላል፡፡

ይህንን በመመለስ በኩል ከአዲስ ኪዳን ላይ በጣም ትንሽ ነገርን ብቻ የወሰደ መሆኑን ለመቀበል እንገደዳለን፡፡ ከዚህም በተዘዋዋሪ መንገድ ሊባል የሚቻለው ነገር ኢየሱስ የተወለደው ያለ ሰዋዊ አባት ነው፣ እርሱም መለኮታዊ ተልእኮ ነበረው፣ ተዓምራቶችን አድርጓል፣ የተወሰኑ ሐዋርያት ነበሩትና ወደ ሰማይ አርጓል የሚሉት ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ መለኮትነቱን መሐመድ ክዷል፣ የመቤዠት ሞቱንም (በውጤቱም ትንሳኤውን) የክርስቶስን ዋና ከሆኑት የወንጌል ዶክትሪኖች ተቃራኒ የሆኑ ብዙ ትምህርቶችን አስተምሯል፡፡ እራሱንም በክርስቶስ ቦታ እንደሆነ በመመኘት እንዲሁም እርሱ የመጨረሻውና ታላቁ የእግዚአብሔር መልክተኛ መሆኑን ሰዎች እንዲቀበሉት ጫና በማድረግ ነበር፡፡ ያንንም በቁርአንና በልማድ ውስጥ አይተነዋል እንዲሁም የአንዳንድ የአዲስ ኪዳን አንቀፆችን መልእክቶችን የተጣመሙ ማጣቀሻዎችን አይተናል፡፡ ለምሳሌም ያህል ገበታው መውረዱን በተመለከተ፣ እንዲሁም መሐመድ እንደሚመጣ ተተንብዮአል በተባሉት ነገሮች ላይ፡፡ ነገር ግን በቁርአን ውስጥ የሚገኝና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ ተወስዷል ሊባል የሚቻል አንድ ብቻ ጥቅስ አለ እርሱንም የምናነበው በቁርአን 7.40 ላይ ነው፡- ‹እነዚያ አንቀጾቻችንን ያስተባበሉ ከርሷም የኮሩ ለነርሱ የሰማይ ደጃፎች አይከፈቱላቸውም፣ ግመል በመርፌ ቀዳዳ እስከሚገባም ድረስ ገነትን አይገቡም እንደዚሁም አጋሪዎችን እንቀጣለን›፤ ይህም ከሞላ ጎደል ቃል በቃል የተጠቀሰው ከሉቃስ 18.25 ላይ ነው ‹ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል አለ።› ከዚህም የሚመሳሰሉ ቃሎች በማቴዎስ 19.24 ላይ ‹ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ።› እና በማርቆስ 10.25 ላይ ‹ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው።›

ከዚህም በላይ በልማዶች ውስጥ ከመልእክቶች የተወሰደ አንድ አስደናቂ ክስተት ይገኛል እርሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለመወሰዱ ምንም ፍንጭ በሌላቸው በብዙ ትክክለኛ አሳቢዎች ሙስሊሞች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነው፡፡ አቡ ሁራይራህ ታላቁ እግዚአብሔር ይህን ቃል ለመሐመድ የተናገረው ነው በማለት መዝግቦ አቅርቦታል፡- ‹ ለኔ ፃድቅ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልብም ውስጥ ያልታሰበውን ነገር አዘጋጅቻለሁ፡፡› እነዚህ ቃላት ከ1ቆሮንቶስ 2.9 ‹ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህእንናገራለን።› ላይ የተወሰዱ መሆናቸው ወዲያውኑ የታወቀ ነገር ነው፡፡ አቡ ሁራይራህ ታማኝ አለመሆኑ ወይንም ይህንን አንቀፅ በመሐመድ እንደተነገረ አድርጎ የመጨመሩ እውነት በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ ነገር ግን በቁርአን 75.22-23 ላይ ያለው አንቀፅ፡- ‹ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው›፣ ማለትም የሚያመለክተው ወደ ውብ እይታ ነው እንዲሁም ወደ 1ዮሐንስ 3.2 እና 1ቆሮንቶስ 13.12 ትዝታ ላይ የሚያመጣ ነው፡፡ እነዚህም ለእርሱ አረፍተ ነገር የእርዳታን ድጋፍን ሰጥቶታል፡፡

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ካየነውና ከአጠቃላይ አንቀፁ ላይ ካለው በጣም ጥንቃቄ ከሚደረግ ምርመራ ተነስተን ለመደምደም የምንመጣው የእውነተኛና ትክክለኛ ክርስትና አስተምህሮ በቁርአንና በእስልምና ላይ የነበረው ተፅዕኖ በአጠቃላይ በጣም ትንሽ የመሆኑን እርግጠኝነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን አፖክሪፋዊ ልማዶችና አንዳንድ ሁኔታዎች እንዲሁም የሐሰት ትምህርቶች የመሐመዳውያንን እምነት በመስራት በኩል ከፍተኛ ምንጭነት እንዳላቸው ግልፅ የሆነ ማስረጃን እየሰጡን መሆኑን በትክክል አይተናል፡፡

የአዘጋጁ ማሰሰቢያ፡

የቁርአንን መጽሐፍ ቅርፅ ስለሰጡት ክርስትያናዊ ማስረጃዎች የቀረበው ምዕራፍ አምስት ስለ ቁርአን ምንነት አስገራሚና ተጨባጭ እውነቶችን አሳይቶናል፡፡ ታሪካዊ የሆኑ ጥናታዊ መረጃዎች ማግኘትና ክፍት በሆነ አዕምሮ ነገሮችን ማመዛዘን ማስተዋል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት እውነቶችንም ለማግኘት መቻል መታደል ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ለአንባቢዎች ነፍስና ሕይወት ምን ያህል ፍቅርና ትኩረት አስደናቂ የሆነ ዕቅድም፣ ሐሳብም እንዳለው ያሳየናል፡፡

በመሆኑም አንባቢዎች እነዚህን ተከታታይ ጽሑፎች እያነበባችሁ እውቀትን ለማግኘትና የዘላለም ሕይወታችሁን ጉዳይ በጥብቅ ልታስቡበት ይገባል፡፡ ከዚህ በላይ በ1ቆሮንቶስ 2.9 ላይ የተጠቀሰው ቃል፡- ‹ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱትያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።› ላይ ያለውን እውነታ ማለትም እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን የዘላለም መንግስቱን እንዴት እንደምታገኙት ማሰብ አለባችሁ፡፡

የእግዚአብሔር መንግስት በኃጢአት ለወደቁና በኃጢአት ከመንግስቱ ለራቁ መዘጋጀቱ አስደናቂ የሆነ ነገር ነው፡፡ የዚያ መንግስት ሁኔታ በዓይን አልታየም አስደናቂ በልብም ያልታሰበ ድንቅ ነው፡፡ ታዲያ ለዚያ ማን ከቶ ማነው የሚበቃው? መጽሐፍ ቅዱስ ያለምንም የተወሳሰበ ውጣ ውረድ የሚናገረው መልእክት አንድ ወጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር መልእክቱን ለሚቀበሉት ያዘጋጀውን መንገድ ለማግኘት ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ መቅረብ ያለባቸው በአዳኝ በኩል ብቻ ነው፡፡ አዳኙ ደግሞ በጣም የሚወደንና እራሱን ለእኛ የሰጠን ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ነው፡፡ እርሱ የሰውን ስጋ ለብሶ እንደሰው የተመላለሰው እኛን ከኃጢአት ዕዳ ነፃ አውጥቶ ለዚያ ድንቅ መንግስቱ ሊያበቃን ነው፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ጥሪ አንባቢዎች ይህንን እውነት ቆም ብለው እንዲያስቡና ለኃጢአታቸው የሞተውን ክርስቶስን በትህትናና በንስሀ መንፈስ ቀርበው ይቅርታን በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር በመቀበል አዲስ ሕይወትን እንዲያገኙ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ መንፈሳዊ ዓይኖቻችሁንም ይክፈትላችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ