በኢትዮጵያ ሃይማኖትና ፖለቲካ ሁለቱ የዘመናት ትግሎች
ትርጉማዊ ቅንብር በአዘጋጁ
መግቢያ
በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሙስሊማዊ የተቃውሞ እንቅስቀሴ ለመረዳትና ዓለም አቀፋዊ ሰፊ ግንዛቤ ለመያዝ እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ምን መልክ ኖሮት እንደቆየና ብዙዎች የማያውቋቸው ውስጣዊ ትግሎች እንዴት እንደተከናወኑ ከታሪክ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ መሰረታዊ እውነቶች ለምንወስደው እርምጃ ድጋፍና ለምንከተለው ፖሊሲ መሪዎች ሊሆኑንም እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የሚቻለው ደግሞ ገለልተኛ የታሪክ ተመራማሪዎች በጥናት ያስቀመጡትን በመመርመር ነው፡፡ ስለዚህም በእነዚህ ተከታታይ የታሪክ አቅርቦቶች ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ ላይ፣ ጥልቅ ምርምር ያደረገው የፕሮፌሰር ኤርሊችን ጥናታዊ የምርምር መጽሐፍ መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ስለዚህም ፕሮፌሰር ኤርሊች በ2007 Saudi Arabia & Ethiopia [ISLAM, CHRISTIANITY & POLITICS ENTWIND] በሚል ርዕስ ያሳተመው ግሩም የታሪክ መጽሐፍ ላይ የተመሰረቱ ታሪካዊ ቅንብሮችን በተከታታይ እናቀርባለን፡፡
በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድና ለቀጣዮቹ ሰባት ምዕራፎች መንደርደሪያ በሚሆነው ምዕራፍ አንድ ውስጥ ከ1974 እስከ 1991 ድረስ የነበረው የመንግስቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ከዚያ በፊት እራሷን አግልላ የነበረችውን ኢትዮጵያን ለእራሷ ሃይማኖታዊ ብሔረሰባዊ ልዩ ልዩ ገፅታ ክፍት እንድትሆን ከዚህም ባሻገር በከፍተኛ ሁኔታ ከመካከለኛው ምስራቅ አጎራባች አገሮች ጋር በጣም እንድትገናኝ አድርጓት ነበር ይላል፡፡ ስለዚህም እስልምናና ሙስሊሞች በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ ሕይወት ማዕከል ውስጥ እንደገቡ ይህም በሁሉም አቅጣጫ ማለትም በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል ዘርፍ ሁሉ ውስጥ እንደበረ የታሪክ ጥናቱ ያቀርባል፡፡ ከዚህ በፊትም እንደተጠቀሰው ሁሉ ፕሮፌሰሩ የተናገረው ኢትዮጵያ “በዓይናችን ፊት እንደገና እየተተረጎመች” መሆኑ በጣም ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ክርስትና የአገሪቱ መለያ መሆኑ ከዚህ በኋላ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ላለፉት ስድስት መቶ ዓመታት እንደነበረው ሁሉ፣ እስልምናም የአገሪቱ የተጎዳና የዳር ዳር ሃይማኖት ሆኖ ሊቀር አይችልም ይልና የሚመጣበት መደምደሚያ “ኢትዮጵያ ትርጉም በሚሰጥ መንገድ እየተቀየረች ነው” የሚል ነው፡፡ የዚህን የፕሮፌሰር ኤርሊችን ታሪካዊ ማስረጃዊ ስጋት እውነት ነውን በማለት ጠይቀን እኛ ወደመደምደሚያ ላይ ልንመጣ የምንችለው አሁን የሚሆኑትን ነገሮችና ታሪክን ጠለቅ ብለን ስናስብ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ፕሮፌሰሩ በዚህ ላይ አላቆመም ሌላ መሰረታዊ ጥያቄን ያቀርባል ኢትዮጵያ እየተቀየረች ያለችው በምን መንገድና ወደየትኛው አቅጣጫ ነው? በአሁኑ ጊዜ ያለው ይህ የእስላማዊ መነሳሳት የማህበረሰባዊ ብዙነትን የሚያውጅ፣ (ማለትም አብሮ መኖርን) የባህልን በብዛት መኖርን፣ በንግድ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መነሳሳትን፣ ንግድን ቴክኖሎጂን አያይዞ ዓለም አቀፋዊ የሆነ እንቅስቃሴያዊ መስተጋብርን አምጥቶ ኢትዮጵያን በብልጥግና የሚያሳድግ ሊሆን ይችላልን? ይልና አማራጩን ግልባጩን ማለትም ሌላውን ጥያቄም እንደሚከተለው ያነሳል፡ ወይንስ የዚህ የእስልምና መነሳሳት የሃይማኖት ግጭቶችን ጦርነቶችን የፖለቲካ የበላይነትን ለመያዝ ወደሚደረግ ትግል አምርቶ ወደ አዲስ አሮጌ ሽክርክር ማለትም እስላም-ክርስትያን ግጭት ያመጣን ይሆንን? በማለት ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች የአገሪቱ ተወላጆችና ተቆርቋሪ ሰዎች ሁሉ ሊጠይቁት የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የአሁኑ የሙስሊማዊ እንቅስቃሴም መታየት ያለበት ሁኔታውን ለግል የፓለቲካ ጥቅም አጋጣሚ ለማድረግ ሳይሆን ለአገሪቱ ዘለቄታ ደህንነት ሲባልም ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ በ2207 ዓም በተጻፈው በዚህ አሁን በምናየው መጽሐፉ ውስጥ በአሁኑ ደረጃ ይህንን ማለት ገና ወጣት ነው ቢልም አሁን ግን ጊዜው እየገፋ ነው መጽሐፉ ከወጣ አምስት ዓመታት ውስጥ እንቅስቃሴው እንደቀጠለ ነው ፍራቻውም ፍራቻ ብቻ ሆኖ ከመቅረት ይልቅ ገሃድ እየወጣና እየገዘፈ ነው፡፡ ስለዚህም ያጠያይቃል እየሆነ ያለው የሚጠቁመው አስቸጋሪ በቀላሉ ሊፈታ የማይችል በአገሪቱ ታሪክ ያተደፈረ ሂደትን ነውና፡፡ መጽሐፉ በተጻፈ በእነዚህ ስድስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ለውጦች፣ ስር የሰደዱ ውስጣዊ ስልቶችና ክንውኖች፤ ቅድመ ዝግጅቶች ተከናውነዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ገና ነው ብለን እናስብና ፕሮፌሰሩ እንዳለው ከአገሪቱ የቆየ አንፃራዊ የሃይማኖታዊ መቻቻል መፅፅናናትን ለጊዜውም ቢሆን እንውሰድ፡፡ ይህም ለብዙ መቶ ዓመታት የኢትዮጵያውያን የጋራ አገናኝ ሆኖ የነበረው ነገር የሃይማኖት ልዩነት ሳይሆን የብሔር፣ የቋንቋ የክልላዊ መለያ እንደነበር ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ የሚለው ኢትዮጵያውያን ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት፤ በተለይም የአጎራባች ሙስሊም አገሮች ጣልቃ ገብነት ለራሳቸው ብቻቸውን ቢለቀቁ ኖሮ አንድ እጅግ በጣም የሚያበረታታ ዕድገት ሊታይ ይችል ነበር ነው፡፡ እውነት ነው ለምንድነው ለብቻችን የማይተዉን? ስለምንስ ጣልቃ ይገቡብናል ብለን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለጣልቃ ገቢዎች ክፍተትን ከመስጠት መቆጠብ እንዴት እንደምንችል ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሂደት በጣም ፈጣን በሆነ መልክ በኢኮኖሚ፣ በባህል እና በስልታዊ ሁኔታዎች ሁሉ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ግንኙነትን በመያዙ የውጭው ተፅዕኖ የማይቀር መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል፡፡ በእርግጥም የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሚኖራቸው ድርሻ ባህርይ ዋናውና ወሳኙ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ በእነርሱ ዘንድ የሚታየው እንዴት ነው? በዚህም እይታ ውስጥ ምን፣ ምን ነገሮች ናቸው የተካተቱት የሚሉት ነገሮችን ሁሉ ማየት ወሳኞች ናቸው፡፡
እስላማዊ መካከለኛው ምስራቅ አገሮችና ክርስትያን ኢትዮጵያ እጅግ ብዙና በጣም ጥብቅ የሆነን ታሪክ ይጋራሉ፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን የሚሰራውና ሙስሊሞች በሙሉ ለኢትዮጵያ ያላቸው የአመለካከት ፅንሰ ሐሳብ የተቀረፀው እና የተመሰረተው በሚከተለው ታሪካዊ እውነታ ላይ ነው፡፡ በመካ የብዙ ጣዖት አምላኪዎች ተቃውሞ በስደት ላይ እያለ መሐመድ የመጀመሪያዎቹን የእርሱን ተከታዮች ለጥገኝነት ወደ ኢትዮጵያ ከላከ በኋላ ክርስትያን ኢትዮጵያ አስጠግታ ጥበቃን አድርጋላቸዋለች፡፡
በዚያ ዘመን በነበሩት የሙስሊሞች ታሪክ ዘጋቢዎች መሰረት ኢትዮጵያንና በእስልምና ላይ ያደረገችውን በተመለከተ የተዘገበው ታሪክ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡
አንደኛው፡ የጀመረው በ615 ዓ.ም መሐመድ ለመጀመሪያዎቹ ተከታዮቹ “ሳሃባዎች” ለሚባሉት መሐመድ ተናገረ በሚለው ላይ የተመሰረተው ነው፡፡ እርሱም በኢትዮጵያ “ማንንም የማይበድል” ፃድቅ ንጉስ አለ ስለዚህም ወደ አክሱም ሂዱ ብሎ አዘዛቸው፡፡ እዚያም በነጃሺ አስሃማ ቤተመንግስት እነርሱ ጥገኝነትን አግኝተው ንጉሱ ነጃሺ ወደ መካ በግድ እንዳይወሰዱ እነርሱን ጠበቃቸው፡፡ ስለዚህም ክርስትያን ነጃሺ የጠቀበው በዚያን ጊዜ የነበረውን እስላማዊ ማህበረሰብ ብቻ አልነበረም ነገር ግን “ሳሃባዎችን” በመንግስቱ ውስጥ ለመጠበቅና እንዲሁም መሐመድንም በመካ ለመጠበቅ እንደሄደ ይተርካል፡፡
ሁለተኛው፡ ሁለተኛው የሙስሊሞች ታሪክ መነገር የጀመረው በ628 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ በዚያ ዓመት መሐመድ በአል-መዲና ውስጥ በተደላደለበት ወቅት የእስልምናን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ጥረት ጀምሮ ነበር፡፡ በመሆኑም ለስምንት አገሮች ከእነዚህም ውስጥ፣ ለፋርስ ንጉስ፣ ለግብፅ ንጉስ፤ ለሶርያና እንዲሁም ለአንዳንድ የአረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ገዢዎች ደብዳቤን ላከ፡፡ የደብዳቤውም መልክእት እስልምናን እንዲቀበሉ የሚል ነበር፡፡ በተመሳሳይም ወቅት ለወዳጁም ለኢትዮጵያ ንጉስ ነጃሺም ተመሳሳይ ደብዳቤን ልኮለታል፡፡ በፕሮፌሰር ኤርሊች ጥልቅ ጥናት መሰረት በሁሉም እስላማዊ ምንጮች የተጠቀሰው የኢትዮጵያው ንጉስ ብቻ ደብዳቤውን ሲቀበል ሌሎቹ አልተቀበሉትም የሚለው እንደሆነ ጠቅሰው (ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ ታሪክ ምንም ፍንጭ የለውም) ይላሉ፡፡ የጥናት ምርምሩ የሙስሊሞች ታሪክ ጸሐፊዎች ያሉትን ሲያቀርብ ንጉሱ ነጃሺ የመሐመድን ሚሽን እንዳደነቀውና እስልምናንም እንደተቀበለው መልሶለታል እንደሚሉ አስቀምጠው፣ ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንደሌለው አበክረው ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁለተኛው ታሪክ ቀጥሎም ያቀረበው ከሁለት ዓመታት በኋላ መሐመድ የነጃሺን ሞት እንደሰማና ከዚያም ለሞተ ሙስሊም እንደሚፀልየው ሁሉ ለእርሱም እንደፀለየለት ነው፡፡
የሁለቱ ታሪኮች መልእክት ለአክራሪ ሙስሊሞች፡
አንደኛው ማለትም የ618 ታሪክ የሚሰጠው መልእክት ለሁሉም ዓይነት ሙስሊሞች አንድ ዓይነት ነው በማለት መናገር ቢቻልም፤ ሁለተኛውና በ628 ዓ.ም የተቀናበረው የታሪክ ክፍል የሚያስተላልፈው መልእክት ሙሉ ለሙሉ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ለአክራሪ ሙስሊሞች፡፡ በዘመናት ሁሉ በአክራሪዎች ሙስሊሞች ዘንድ ማለትም በመካከለኛው ምስራቅ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ አራማጆች ዘንድ ታሪኩ የተተረጎመው እንደሚከተለው ነው፣ “እስላም አል-ነጃሺ” ማለትም “እስላም የሆነው የኢትዮጵያው ንጉስ” ኢትዮጵያ የ”እስላም ምድር” አንዷ አካል ወይንም “ዳር አል-እስላም” ናት የሚለውን ፍልስፍና ሰጥቷል፡፡ እነርሱም የሚከራከሩት ሙስሊሙ አል-ነጃሺ በጦር አዛዦቹና በካህናቶቹ ክዳት (ከድተውት) ተገድሎ እንደሞተ ነው፡፡ ስለዚህም በእስላሞች ዘንድ ያለው አመለካከት ኢትዮጵያን የሚያቀርበው እስልምና በመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈትና ውድቀት ያጋጠመው ቦታ ተደርጋ ሲሆን የኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ክደት የተሞላበትና የከሃዲነት እና ሕጋዊ ያልሆነ ታሪክን ነው፡፡ ስለዚህም ክርስትያን ኢትዮጵያ እስልምና በአፍሪካ ውስጥ ያለውን መስፋፋት ያገደችና በአገሪቱ ውስጥም ያሉትን (የራሷን) ሙስሊሞች የምትጨቁን አገር ናት ነው፡፡ በእስልምና አክራሪዎች ዓይን ፊት ኢትዮጵያ እንደገና ልትድን የምትችለው እንደገና ሙስሊማዊ መሪ በማስቀመጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ለብዙ መቶ ዓመታት የእስላም አል-ነጃሺ መፈክር የሚናገረው የኢትዮጵያ ንጉስ ሙስሊም ነበርና ስለዚህም አሁንም አገሪቱ በእስላም የግድ መገዛት አለባት ነው፡፡ ይህም መፈክር በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያሉትንና የኢትዮጵያን ክርስትያንነት ለመርገጥ (በመበቀል (በበቀል) ለማጥፋት) የሚፈልጉትን ሁሉ ያገለገለ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉትን ሙስሊሞች የፖለቲካ መሪነታቸው ላይ እንዲንፈራጠጡ በከፍተኛ ደረጃ የሚያበረታታ መሆኑን የፕሮፌሰር ኤርሊች ጥናት አበጥሮ ያሳያል፡፡
የተለያዩ አገሮች ለኢትዮጵያ ያነበራቸው አመለካከት፡
“በኢትዮጵያን አትንኳት” እና “በእስላም አል-ነጃሺ” የሚሉት ሁለት የተለያዩ ርዕዮተ አለማዊ አመለካከቶች ኢትዮጵያ በአጀንዳ ላይ በምትቀርብበት እስላማዊ ውስጣዊ ውይይት ሁሉ ላይ የሚቀርቡት ዋናዎቹ ርዕሰ ጉዳዮች እንደሆኑ የታሪኩ መጽሐፍ ያመለክትና የሚከተሉትን ምሳሌዎች ያሳያናል፡፡
የሱዳኑ ማህዲ ጦርነት፡
ለምሳሌም ያህል የሱዳኑ ማህዲ በ1885 በመጀመሪያ ኢትዮጵያን በተመለከተ ይከተል የነበረው መስመር “ኢትዮጵያን አትንኩ” የሚለውን ነበር እንዲሁም ለጊዜውም ቢሆን እርሱን ይሰብክ ነበር፡፡ እርሱና የእርሱ ተከታይ ካሊፋው ቆየት ብለው መስመራቸውን በመቀየር በንጉሱ በአፄ ዮሐንስ 4ኛው ላይ የጂሃድን ጦርነት አወጁ፣ (1872-1889) ይህንንም ያደረጉት የእስላም አል-ነጀሺን መንገድ ንጉሱ እንዲከተልና እስላም እንዲሆን ጥሪ በማቅረብ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል፡፡
የሙሶሊኒ ወረራ ክስተት፡
ኢትዮጵያ በቤኒቶ ሙሶሊኒ በ1935 ጥቃት እንደሚሰነዘርባት በታቀደበት ጊዜ በዓረቡ ዓለም ሕዝብ ውስጥ በከፍተኛ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ሆነው ይፍተለተሉ የነበሩት እነዚህ ሁለቱ ፅንሰ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ እራሳቸውን ከኢትዮጵያ ትግል ጋር አንድ ያደረጉት አረብ አገራት መሐመድ ስለ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የተናገረውን ውለታ ሲያነሱ፤ ምስጋናና ጥያቄዋም ተቀባይነት እንዳላት ሲናገሩ፤ ፋሺስት ሙሶሊኒን የወገኑት ግን ግምታቸው የነበረው ሙሶሊኒ “የእስላም ነጃሺን” መንግስት በኢትዮጵያ በመጨረሻ መልሶ ያቋቁማል የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡ ይህን በቅርብ በምናወጣው “የሙሶሊኒ ግመሎች” ርዕስ ማለትም በሌላ ጽሑፍ የምንመጣበት ቢሆንም በዚያን ጊዜ የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን የእስላም አገር ለማድረግ በገባው ቃል መሰረት 70,000 የሙስሊም ወታደሮች ከአገር ውስጥና ከውጭ ተውጣጥተው ከፋሽስቱ ጎን ተሰልፈው አገሪቱን ወግተዋል፡፡
ግብፅና ኢትዮጵያ፡
ከኢትጵያ ጋር ብዙ ታሪካዊ ትስስር ያላትም ግብፅ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚደረገው ውስጣዊ ግብፃዊ እስላማዊ ውይይት ሁሉ ላይ ከ1250 - 1570 በነበረው የማሙሉክ ዳይናስቲ እና እስከ ሆስኒ ሙባረክ 1981 ድረስ ትከተል የነበረው ሐሳብ በእነዚህ ሁለት ፅንሰ ሐሳቦች ዙሪያ የሚውጠነጠን የነበረ መሆኑን የነፕሮፌሰር ኤርሊች ታሪክ ያሳየናል፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን እምነት እና የኢትዮጵያን እስልምና ሁለቱንም በመቅረፅ በኩል ታላቅ ሚና እንደተጫወተች ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ የአባይን ውሃ በተመለከተ ግብፆች ባላቸው ስጋት መሰረት ሁል ጊዜ ሰላማዊውን መንገድ “ኢትዮጵያን አትንኩ” የሚለውን ለመከተል የሚመርጡ የነበሩ ቢሆንም እንኳን ምናልባት አባይን በተመለከተ አንድ እርምጃ ወይንም እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ በኩል ቢከሰት “የእስላም ነጀሺ” ፅንሰ ሐሳብ ግን ሁልጊዜ በጠረጴዛቸውና በአክራሪዎቻቸው ውስጥ ለጦርነት ለመንቀሳቀስ ዝግጁ እንደነበረ መጽሐፉ ያስረዳል፡፡ የሆነው ሆኖ ባፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት ውስጥ ግብፅ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላት ጣልቃ ገብነት አብቅቶ ዋናውን ሚና የያዘቸው ሳውዲ አረቢያ ሆና እንደቆየች የዚህም ምክንያት ከዚህ መጽሐፉ አድማስ በላይ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
ሳውዲ አረቢያና ኢትዮጵያ
እንግዲህ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ያለው የሳውዲ ገንዘብ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለውና በአሁኑ ጊዜ ለሚታየው እስላማዊ እንቅስቃሴ ሁሉ ከበስተጀርባ ሆኖ የሚመራው እርሱ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ በመጽሐፉ ላይ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ቁጥር የሌላቸው የብዙ መስጊዶች ግንባታ፤ የቁርአን ማዕከሎች ግንባታ፤ የእርዳታ ድርጅቶች እንቅስቃሴን ለምሳሌም ወላጅ የሞቱባቸውን ድርጅቶች የሚመራው፤ የአረብኛ ቋንቋ መስፋፋት የመጽሐፍት ትርጉምና ስርጭት ስራውን የሚሰራው የሳውዲው ገንዘብ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የሃጂ ጉዞ መስፋፋት፤ የኮንፈራንሶች ዝግጅቶች፤ እንዲሁም የሰባኪዎች ስልጠናዎች፤ ወደ እስልምና ለተለወጡት በየወሩ የሚያስፈልጋቸውን ደመወዝ በመስጠት እንዲሁም ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥር ብዙ ናቸው የሚለውን ክርክርና አሉባልታን ማስፋፋት እና ማሰራጨት ሁሉ በጥልቀትና በትጋት የሚደረጉት በሳውዲ ገንዘብ እንደሆነ ጽሑፉ አስቀምጧል፡፡ በእርግጥ ፕሮፌሰር ኤሪሊች እንደሚለው በጣም ብዙው የሳውዲ ጥረት ትኩረትን የሰጠው በኦሮሞ ሕዝብ እና በደቢባዊው ክልል ላይ ነው፡፡ ይህም እስልምና በተከከለችው ከተማ በሐረር ዙሪያ ላይ ስለሚሽከረከር ቢሆንም፣ ነገር ግን በክርስትያኑ ማዕከላዊ አካባቢዎችም ላይ ተፅዕኖን ለማድረግ ትልቅ ትኩረት ጥረትም ይደረጋል፡፡ ሳውዲ አረቢያም በኢትዮጵያ ውስጥ እያሳየች ያለችው ቅስቀሳ የትምህርትን መስፋፋትና አጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ ግልፅነትን እንደምትደግፍም ሆና እንደሆነና ይህም በግልፅ እንደሚታይ ተገልጧል፡፡
ስለዚህም የሳውዲ መጽሐፍት ይህንን ርዕዮተ ዓለም ለማስፋፋት ከበስተጀርባ በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ አንዱና ዋናው የሳውዲዎች የመከራከሪያ ሐሳብና በግልፅ እየቀረበ ያለው እንደሚከተለው ነው፡
- ክርስትና በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ነው ይህም የሚደረገው በምዕራባዊ ኢምፔሪያሊስቶች ነው፡፡ እነርሱም ከዚህ በፊት አህጉሪቱን በቅኝ ግዛትነት አስጨንቀዋት ነበር፡፡
- ክርስትያኖቹ ምዕራባውያን ኢምፔሪያሊስቶች እስልምናን ለማግለል ከፍተኛ ጥረትን ያደርጋሉ ነገር ግን እስልምና በተፈጥሮው በመቻቻል መርሆ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በአገሪቱ ውስጥ ሊሰፍን ለሚገባው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ከፍተኛ እገዛን ያደርጋል የሚል ዘመቻ ነው፡፡
- የፕሮፌሰር ኤሪሊች መጽሐፍ እንደሚለው፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰራጨ ያለው ዋሃቢዝም ማለትም የሳውዲው አክራሪ እስልምና ትምህርት ከዚህ ከሚባለው የቅስቀሳ ሐሳብ ጋር በጣም የተቃረነ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በአገሪቱ ውስጥ በሳውዲ መራሹ ዋሃቢዝም የሚሰጠው ቅስቀሳ የአፍ ብቻ፤ የውጭ፤ ለተቀባይነት ብቻ የሚደረግ ቅስቀሳ ብቻ ነው ይለናል፡፡
ልዩ ልዩ የሳውዲ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ለዚህ ጥረት ከፍተኛ ድጋፍን አድረገዋል ብዙዎቹም በሙስሊም ዓለም አቀፍ ሊግ ጥላ ስር የተደራጁ ናቸው (ራቢታት አል-ኣላም አል-እስላም)፡፡ ይህ ድርጅት የተመሰረተው በ1962 ሲሆን እስላማዊ ጥሪን ለመደባለቅና እስላማዊ ትምህርትን ለማሰራጨት ጥሪን ለማድረግ የተመሰረተ ነው፡፡ ድርጅቱ የሚመራው በሃይማኖታዊ ድርጅቶች ሲሆን በበላይ የሚቆጣጠረውና በገንዘብ የሚደግፈው የሳውዲ መንግስት ነው፡፡ አሁንም የስርዓቱ አካል ቢሆንም ከ1990 ጀምሮ የሙስሊም ዓለም አቀፍ ሊግ የሳውዲ አረቢያን በጣም አክራሪ ክንፍ የሚመራው እርሱ ነው፡፡ የሳውዲን ንጉሳዊ አገዛዝ በመገዳደርና እስላማዊ ሞራልን በጣም በጠነከረ መልኩ እንዲተገበር በማድረግ ይህ ድርጅት ቢያንስ በተዘዋዋሪ መንገድ ዓለም አቀፍ እስላማዊ አክራሪነትንና ኔት ወርክን በጣም አጠናክሯል፡፡
ሳውዲዎች ለኢትዮጵያ ሃይማኖት፡
ሳውዲዎች ስለ ኢትዮጵያ የሃይማኖት አለም ምንድነው የሚያስቡት? የሚለውን ጥያቄ የታሪክ ምሁሩ በመጽሐፉ አንስቶ እንደሚከተለው ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ ክፍትነት ውስጥ (ሁሉን አቀፍነት) ውስጥ የእስልምናን ማንሰራራት እንደ አንድ ክፍል ይመለከቱታል ወይንስ እስልምና በአገሪቱ ውስጥ ድል አድርጎ እንዲቀመጥ ይሰራሉ? በታሪካዊ ኢትዮጵያ ላይ ዋሃቢዎች ያላቸው ዋነኛው ፅንሰ ሐሳብ ምንድነው? በሳውዲ አረቢያው መንፈሳዊ መስራች ዘንድ ጎረቤት የሆነችው ክርስትያን መንግስት እንዴት ነው የምትታየው? ከሃይማኖት ልዩነት ባሻገር ኢትዮጵያ የምትታየው እንደ “የፅደቅ አገር” ተደርጋና ተቀባይነት ያላት ዋጋ ለመኖር መብት ያላት ተደርጋ ነውን? ወይንስ ኢትዮጵያ የአሰቃቂው የመጀመሪያ እስልምና ሽንፈት የታየባትና ልትድንም የምትችለው በእስላማዊነት ብቻ እንደሆነ ተደርጋ ነው? ወይንስ ሳውዲዎች ልክ እንደሌሎች አጎራባች እስላማዊ አገሮች ወዲያና-ወዲህ በሚል ጥንዳዊ የድብልቅ አቀራረብ ጋር በመሆን ከታሪካዊ ለውጥ ጋር የሚለዋወጥ የፅንሰ ሐሳብን ትኩረት ይዘዋልን? በ1990ዎቹ ውስጥ በሳውዲ ወደ አገሪቱ ውስጥ እንዲሰርግ የተደረገውና በአፍሪካ ቀንድ ያለው ከአልቃይዳ አክራሪነት እንቅስቃሴ በስተጀርባ ያለው ምንድነው? የአልቃይዳ አሸባሪነት እና በእርሱ የእርዳታ ድርጅቶች (ምግባረ ሰናይ) ለዋሃቢዝም ሌላው የመስፋፋት ገፅታዎች ነበሩን? እነዚህን ወሳኝ የሆኑ ጥቄዎችን መመልከት ባለፉት ሰባት አስርተ ዓመታት ውስጥ የሳውዲን ስልትና የሃይማኖት ምስቅልቅል ሁኔታን ማጤን በጣም ጠቃሚ መሆኑን መጽሐፉ ይጠቁማል፡፡
ኢትዮጵያና የራሷ ሚና፡
ከዚህ የሚቀጥለውም ነገር ደግሞ የራሷ የኢትጵያ ሚና ነው በእነዚህ ተንቀሳቃሽና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ግንኙነቶች ውስጥ የኢትዮጵያ የራሷ ሚና ምንድነው የሚለው ቀጣይ ሊታይ የሚገባው ነገር መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያነሳል፡፡ ክርስትያን ኢትዮጵያ ማለትም ዋናው ባህልና አገሪቱን የሚቆጣጠረው የምሁራኑ ቡድን እራሱም የራሱን አመለካከት (ወይንም አስተያየት) አዳብሯል፡፡ ይህም ለእስላማዊው መካከለኛ ምስራቅ ሌላነት፡፡ የክርስትያቹ ፅንሰ ሐሳቦች በእኩል የነበሩት ጥንዳዊና በተመሳሳይም መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡ እነርሱም እራሳቸው በነባራዊው ሁኔታ የሚቀረፁ ነበሩ ይህም ከመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ ጋር አብሮ ተያይዞ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በጣም ጠልቆ የገባም ፍርሃት ነበር፤ አሁንም በአንዳንዶችም ዘንድ አለ፤ ይህም በአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተፈጠረው ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት ጠባሳ ነው፡፡ ፍርሃቱምን እንደሚከተለው መጽሐፉ አስቀምጦታል፤ “አገሪቱ ለመካከለኛው ምስራቅ ከፍት መሆኗ እስላማዊ ሚዛን አቀንቅኖ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የክርስትያን መንግስትን ወደማጥፋት ይሄዳል የሚለው ፍርሃት ነው” ይለናል፡፡ ይህ የጦዘ ሁኔታና አመለካከት ልዩ ትንተናና ግንዛቤ ሊሰጠው የሚገባው እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ያሳያል፡፡
ቀጥሎም የሚያስገነዘበው ኢትጵያዊው ክርስትናም ይሁን የሳውዲው ዋሃቢዝም ከአለም ዓቀፍ ሃይማኖት ጋር የተያያዙ የነበሩ ቢሆኑም እንኳን እንዲሁም አሁንም ወደፊትም ቢያያዙም የራሳቸውን አካባቢያዊ መለያና ባህል እያሳዩ እንደሆኑ እንዲሁም ጥብቅ ከሆነ የፖለቲካ ስርዓት ጋር ውስጣዊ ግንኙነት እንዳላቸው ነው፡፡ ስለዚህም በሳውዲ አረቢያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ሁለቱም ካላቸው ሃይማኖታዊ አመለካከታቸውና ለውጥ ባሻገር ሊተረጎም አይችልም፡፡
ይህ ነው ኢትዮጵያ የራሷን ሚና ለመወጣት በምትሄድበት ጊዜ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሌላ ማለትም ያልነበረ ትርጉም ውስጥ ወደ መዝቀት ችግር እንዳትወድቅ መጠንቀቅ የሚኖርባት፡፡ ለዚህም ነው ጋዜጠኞች የፖለቲካ ድርጅት አባላት እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ባለፉት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጊዜ ተቃውሞውን በግልብ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ብቻ በማድረግ የሰጡት ድጋፍና ልዩ ል መግለጫ ትክክል አይደለም የሚባለው፡፡ ምክንያቱም በማያውቁትና ስር ድረስ ባላጠኑት ጉዳይ ላይ ሚዛን ባጣው ታሪካዊና ሃይማኖታዊ አዲስ የኢትዮጵያ ትርጎማ ላይ ተባብረዋልና፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞችስ?
ሌላው መሰረታዊ እውነታ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች በራሳቸው በኩል ያለው ሁኔታ ነው፡፡ በክርስትያን መንግስት ውስጥ ባላቸው የራሳቸው ቦታና በአካባቢው ተፅዕኖ፣ ከአካባቢው በሚመጡ መልእክቶች፣ እና በመካከለኛው ምስራቅ አብሮ ተጋሪዎች መካከል ሆነው የራሳቸውን አመለካከትና ፅንሰ ሐሳብ አዳብረዋል፡፡ ስለሆነም ይላል የፕሮፌሰሩ ጽሑፍ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያሉበትን ጊዜያዊ ምስቅልቅሎች በተመለከተ ያላቸውን ታሪካዊ ገፅታዎችን እንዳስሳለን ይላል፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች “ፃድቅ” እስከሆነ ድረስ ያሉበትን ክርስትያናዊ መንግስት በመቀበል (በመሐመድ) እንደታዘዙት ሊኖሩ ይችላሉን? ወይንስ የእስላም አል-ነጃሺ ፅንሰ ሐሳብን ተከትለው የፖለቲካዊ እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ድል እንዲያደርግ ይታገላሉ? እነዚህ ጥያቄዎች ናቸው አሁን ያለውን የእስልምና እንቅስቃሴና አጠቃላይ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ እንድንቃኝ የሚያደርጉን፡፡
ፕሮፌሰር ኤሊሪች እንደሚለው በአገሪቱ ውስጥ ባለው አገር አቀፍ አጀንዳ ላይ ምናልባትም ብቸኛውና ጊዜያዊው አጀንዳ መሆን የሚችለው ነገር ውስጣዊ ኢትዮጵያዊ እስልምናዊ እንቅስቃሴ ነው፤ ምክንያቱም በአጠቃላይ እስላማዊ ክርስትያንና፤ አረባዊ አፍሪካዊ የውይይት አጀንዳ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ እስልምናን በተመለከተ ከሚነሳው ጥያቄ የበለጠ ዋና አጀንዳ የለም ሊኖርም አይችልም የሚለው የፕሮፌሰር ኤሪሊች ታሪካዊ ድምዳሜ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህም አሳሳቢነቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ናቸው፣ ለምን የተቃውሞ እንቅስቃሴ አስነሱ፣ የተቃውሞው እንቅስቃሴ ስር ከሰደደ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የርዕዮተ ዓለም ትግል ጋር የተቆራኘ ነው ወይ? የሚሉት ጥቄዎች መነሳት ግድ አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳለው ሁሉ ለሁለት የተከፈሉ ናቸው፣ ዋሃቢዝምን የሚደግፈውና የሳውዲ መጠቀሚያ ለመሆን የሚፈልገው በብዘት ወጣቱን የያዘው ቡድን ነው፡፡ ሌላው በጣም አናሳው የ”አል-አህበሹ” ወይንም “ኢትዮጵያውያኖቹ” ነው፡፡
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተገለፀው ሁሉ የአሁኑ ጊዜ የሙስሊሞች ተቃውሞ በቀጥታ የተያያዘው አል-አህበሽን ከሚቃወመውና በሌላ አባባል ከዋሃቢዝም ደጋፊ ነው፡፡ የዚህ ቡድን እንቅስቃሴ ዓላማው ግልፅ ነው፣ ይህንንም ዓላማውን በተለያዩ የድረ ገፅ ጽፉፎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስብሰባዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን ድረ ገፅ እና እንዴትም አል-አህበሽን የሚቃወም ስር የሰደደ ስራ እንደሚሰራ http://www.ethioislamicart.com/4632492546274941.html በጣም ግልፅ ነው፡፡
በፕሮፌሰሩ ታሪካዊ መጽሐፍ ውስጥ ለተቀመጠው ጥያቄ ትክክለኛው መልሱ አሁን ያለው የሁለቱ ድርጅቶች ትግል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እና የሁለቱን ድርጅቶች ትግል እና ርዕዮተ ዓለም እና የሚመጣውን ውጤት ከመረመሩ በኋላ በጣም ቢዘገይም የወሰዱት እርምጃ ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን አገሪቱን ከሚመጣው ከፍተኛ የአክራሪዎች አደጋ አድኗት ሕዝቡ እንዲነቃ በጉዳዪ ላይ እንዲወያይም ታሪክንም እንዲዳስስ መንገድን ከፍቷል፡፡
በእርግጥ የመንግስት እርምጃ በሃይማኖት ላይ ጣልቃ እንደመግባት የተቆጠረና ብዙዎችን ያስኮረፈ እንዲሁም ደግሞ ለፓለቲካ ግል ጥቅም አገልግሎት ላይ የዋለ ቢሆንም ወደፊት ታሪክ በሚመረመርበት ጊዜ አስፈላጊ የነበረ መሆኑን ብዙዎች ይገነዘቡታል፡፡
ካኮረፉትና የራሳቸውን ጽሑፍ ለመጻፍ ከተነሱት ሰዎች መካከል ይህ የዚህ ጽሑፍ አቀናባሪ የጠቀሰው የአብደላ አደም ተኪ ጽሑፍ ይገኛል፡፡ ይህንን ጽሑፍ በሚከተለው ድረ ገፅ ማግኘት ይቻላል፤ https://docs.google.com/file/d/0ByxJ0rgpLftXM3lDR0h4MU1ZVEU/edit?pli=1 እንዲሁም ከዚህ በፊት የተጠቀሱትን ሌሎች ድረ-ገፆችን ማየት ጠቃሚ ነው፡፡
አጠቃላይ ግንዛቤ
በምሁራኖች ዘንድ ያለው በጣም አስደናቂው ዋነኛ ትግልና የአሁኑን ዓለም፤ በአጠቃላይ እስልማዊውን ዓለም ለሁለት የከፈለው ትግል በእስልምና ዋሃቢስቶች አቀንቃኞችና በ“ኢትዮጵያዊያኖች” ወይንም “አል-አህበሾች” በሚባሉት መካከል ያለው ስር የሰደደ ትግል ነው፡፡
አል-አህበሽ ማዕከል ያደረገው በቤይሩት ነው በዓለም ዙሪያ ሁሉ ቅርንጫፎችና ቢሮዎች አሉት የሚሰብከውም፡ “እስልምናና-ክርስትና” በመካከለኛው ምስራቅ፣ በዩሮፕ፣ በአሜሪካ እና በየትም ቦታ አብረው በሰላም መኖር እንደሚችሉ ነው፡፡ የእነርሱ ተቃራኒዎች የሆኑት ዋሃቢስቶች እነርሱን ይከሷቸዋል ይህም አጠቃላይ በሆነ ጦርነት ነው በኢንተርኔት፣ በጋዜጦች በበራሪ ወረቀቶች በመጽሐፍት በስብከቶች እንዲሁም በፋትዋ ጭምር ነው፡፡ የሚከሷቸውም የእስልምናን እውነተኛ ተፈጥሮ አጣመዋል በማለት ነው፡፡
ሁለቱም ቡድኖች የሚመሩት በሽማግሌዎች ሼኮች ነው፤ ሁለቱም የወጡት ከኢትዮጵያዊቱ የእስልምና ዋና ከታማ ከሐረር ነው፡፡ ስለዚህም የእነዚህን ሁለት ሼኮች ታሪካዊ ዕድገት በሰባት አስርተ ዓመታት ውስጥ ከኢትጵያና ከሳውዲ ጋር በተያያዘ ሁኔታ መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው ይላል ፕሮፌሰሩ፡፡ ጉዳዩም የሚመለከተውና የሚያጠቃው ሁለቱን አገሮች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ዓለማችንን ጭምር እንደሆነ በታሪኩ ምርመራ ላይ አስቀምጧል፡፡
የዚህ ድረ ገፅ አዘጋጆች እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ አምድን የከፈቱትም ለዚህ ነው፡፡ ጉዳዩ አንዳንድ ላይ ላዩን ለሚመለከቱ ሰዎች ቀላል ይምሰል እንጂ ጥልቅና በጥልቀት ሊታሰብበት የሚገባ የወደፊቱን ኢትዮጵያን ታሪክ አቅጣጫና ሕዝብ ኑሮ የሚመለከት ነው፡፡
በታሪክ እንደታየው ኢትዮጵያ እስልምናና ክርስትና በመጀመሪያ በአገር ደረጃ የተገናኙባት አገር የመጀመሪያዋ ናት፡፡ የክርስትናና እስልምና ግንኙነቶች በጣም ወሳኝ ነጥቦች እየሆኑ በሄዱ ቁጥር፤ በብዙዎች ዘንድ ብዙውን ጊዜ እንደ ዓለም አቀፍ “የስልጣኔ ግጭቶች” ተደርጎ እንደሚቆጠረው አይደለም ይልና ፕሮፌሰሩ የሚያበክረው የእኛ “የሳውዲ-ኢትዮጵያ” እውነተኛ ታሪክ አዲስ የሆነ ገፅታን የሰጠንና ትክክለኛ መረዳት ላይ ያመጣናል የሚል ሃሳብ አለው፡፡ ማለትም የምዕራም ምስራቅ የስልጣኔ ግጭት ያለፈ ጉዳይ ነው የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ነው የሚያራምደው፡፡
እርሱም የጥንታዊውን “ክርስታያናዊ-እስልምና” ውይይትንና ጥንታዊ ቅርስ ይሰጠንና እንዲሁም እንዴት ወደ “ምዕራብ-ምስራቅ” ወጥቶ እንዳደገም ያሳየናል፡፡ የኢትዮጵያ ክርስትና የመጣው ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምስራቃዊ ክርስትና ሲሆን ከ334 ዓም እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ የመንግስት ሃይማኖት በመሆን ቆይቷል፡፡ ሳውዲ አረቢያ የተመሰረተችው ከአስራ ስምንተኛው መቶ ዓመት በገዢ ቤተሰቦች መወሰድ ጀምሮ እጅግ ግትር በሆነ ቁርአናዊ ትምህርት ላይ በመመስረት ነው፡፡ የሁለቱም መንግስታት (የኢትዮጵያና የሳውዲ) ባህሎች እንዲሁም ማህበረሰቦች የቆዩት ጥብቅ በሆነ ታሪክ ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ነው ስለዚህም የእነርሱ ዘመናዊ ሁኔታ እና ግንኙነት የቀጠለው በእነርሱ በራሳቸው በሆነ ክርስትያን-እስላም ፅንሰ ሐሳቦች ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ታሪኩ ያስረዳል፡፡
የእኛ ትንተና የሚሽከረከረው በማለት በመጽሐፉ ላይ ፕሮፌሰሩ ያቀረበው በወሳኝ የሃይማኖት ቅርሶችና በተጨባጭ የዓለም አቀፍ ፓለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚሽከረከረው ቀጣይ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡ ከቀይ ባህር ማዶ ያሉት ሙስሊሞችና ክርስትያኖች ሁሉ እንደ የሰው ልጅ ቡድን አባላት ሁሉ የቀጠሉት ለየራሳቸው ታሪካዊ ምንጭና የጋራ የሆነ ታሪካዊ ትውስታ፣ ፅንሰ ሐሳብ፣ ምሳሌና ምስሎች ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮችም አመለካከቶችንና ፖሊሲዎችን ሲመሰርቱ ጭምር ያገለገሉ ናቸው፡፡
ስለዚህም በተከታታይ በተለያየ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አጠናቅረን የምናቀርበው የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ የሚያሳየን ከ1930 እስከ 2005 ባሉት ዓመታት ውስጥ የሳውዲ-ኢትዮጵያን ግንኙነቶች እንዴት እንተገለፁ ነው፡፡ ይህ አስፈላጊ የሆነው አሁን ያለው ሁኔታ እንዴት እና በምን ሁኔታ አድጎ እዚህ እንደደረሰ እና ለዚህም ሁሉ ታሪካዊ እውነታዎች የውስጣዊው ክርክርና ሃይል ምን እንደነበረ ያሳየናል፡፡
መጽሐፉ ይህንን ታሪካዊ እድገት ለመፈልፈል በጣም ጠቃሚ የሆኑትን ጽሑፎች፣ የጋዜጦች ጽሑፎች ንግግሮች የትምህርት ቤቶች መማሪያ መጽሐፍት መንግስታዊ መግለጫዎችና እና ሰርኩላሮች ይቃኛል እንዲሁም በጣም የቅርብ ጊዜውን የኢንተርኔት ክርክሮችን ይዳስሳል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮችና ከገለልተኛ የታሪክ ምሁራን መገንዘብ ነገሮች እንዴት እንዳደጉ እና እዚህ እንደደረሱ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን አገሪቱና አገር ወዳዱ ሕዝብ በዚህ ላይ ተመስርቶ ለወደፊቱ ኢትዮጵያ ምን መደረግ እንዳለበት ቆም ብሎ እንዲያስብ ይረዱታል፡፡
ፕሮፌሰር ኤሪሊች በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ውስጥ ያስቀመጠው፡ የዚህ ታሪካዊ ጥናት መሰረታዊው የመጨረሻ ነጥብ የሚያሳየው ነገር በዚህ የፖለቲካና የሃይማኖት ውርስ ውስጥ ማንኛውም (ያልተጠበቀ) ነገር ሊሆን እንደሚችልና ማንኛውም ነገር ሊለወጥ እንደሚችል ነው በማለት ነው፡፡ ጥንታዊ የሆነው በጥብቅ የተያዘው የፅንሰ ሐሳብም ምንጮች እንኳን ሳይቀሩ ሊተረጎሙና እንደገናም ሊተረጎሙ የሚችሉ እጅግ በጣም ስፋት ያላቸው መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ቀጥሎም “ለእኛም” ይልና የእስላማዊ-ኢትዮጵያ ጉዳይ በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው ምክንያቱም ጥንታዊው፣ መሰረታዊው (የመጀመሪያው) የመሐመድ-ነጃሺ ታሪክ ጥንድ የሆኑ ውርሶችን ይሰጠናልና፡፡ በሁለቱም በኩል ያሉት ታሪክ አስተካካዮች (ቀራፂዎች) እንደምናየውም ሁሉ የታሪክ እስረኞችና እንደሁም ደግሞ የታሪክ አዋቂዎች ናቸውና (ሁለቱንም) እነርሱም በጥንት ውርስ ነው ይመሩ የነበሩት፤ ነገር ግን ይልና በፍላጎታቸው መሰረት የመረጡትና ሕጋዊ ለማድረግ የፈለጉት (የሚታገሊለትም እንደማንኛውም ፖለቲከኛ) የሚፈልጉትን ነገር ነውና በማለት ከታሪክ ባገኛው ሐሳብ ላይ ተመስርቶ የግል ሐሳቡን ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የፕሮፌሰሩ ሐሳቦች በሜዳ የሚጣሉ ሊሆኑ አይገባቸውም፡፡ ክርስትናም ሆነ እስልምና ፖለቲካ ከተደረገ በተለይም የዋሃቢው አዝማሚያ እንኳን ለኢትዮጵያ ለማንም አይበጅም፡፡
ወደ ምዕራፍ አንድ መደምደሚያ ላይ ሲመጣም ፕሮፌሰሩ ከላይ የተናገረውን ሐሳብ እንደገና አንስቶ ሌላም ገፅታን ይጠቁማል እንደሚከተለው በመናገር፤ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ግጭት አንዳዶች እንደሚሉት “የስልጣኔ ግጭት” ይመስላቸዋል ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ያለው ዋናው ግጭት ክርስትና-ከእስልምና ጋርም እንኳን አይደለም ነገር ግን “እስላማዊ - ከእስላማዊ” ጋር ነው እንጂ፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ጊዜ ያለው ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት ዋናው ምክንያት በምዕራባዊው ክርስትና እና በእስልምና መካከል ያለው ሳይሆን በእስልምና ውስጥ ያለው ውስጣዊ ክርክርና ግጭቶች የተነሳ ክስተት ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ላይ የሚታየው ጥናትም የሚደግፈው ይህንን እውነታ ነው፡፡
የተከበራችሁ አንባቢዎች ሆይ ይህ ተከታታይ ጽሑፍ መጠነኛ ታሪካዊ ግንዛቤን ይሰጣል በማለት ከገለልተኛ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኤሪሊች መጽሐፍ ላይ ያቀናበርነው ነው፡፡ ይህ ታሪካዊው መግቢያና የጥናቱ መዋቅር ነው፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ውስጥ ታሪኮች እየገባን እንሄዳለንና በትግስት ተከታተሉን፡፡
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ