ቁርአን - የተቃርኖዎች መጽሐፍ 

በ ዳንኤል

ብዙ ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ስህተቶችና ግጭቶች መኖራቸውን ሲነገሩን ኖረዋል፡፡ እነ አሕመድ ዲዳትን የመሳሰሉ ሙስሊም ጸሐፊዎች እንዲያውም የስተቶቹን ብዛት ከሃምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ያደርሱታል፡፡ (መቶ ሺህ ስህተቶች ማለት በግምት በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ወደ ሦስት ስህተቶች ማለት ነው!) ለእንደዚህ አይነቶቹ መሰረት የለሽ ክሶች ክርስቲያን ምሁራን በበቂ ሁኔታ ምላሽ ሰተዋል፡፡ ነገር ግን ሙስሊም ሰባኪዎች በሚችሉት አቅም ሁሉ የሌላውን የእምነት መጽሐፍ እያብጠለጠሉ እና እየወረፉ የራሳቸውን ግን እንደ አይነኬ መቁጠራቸው በኃቀኝነታቸው ላይ ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ እነዚህ ሰባኪዎች ቁርአን እርስ በእርሱ የተስማማና ምንም አይነት ግጭት እንደሌለበት በመመጻደቅ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ቁርአንም ስለራሱ በቁርአን 4.82 ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል፡-

      “ቁርአንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡”

በዚህ ጥቅስ መሠረት በቁርአን ውስጥ ምንም አይነት ተቃርኖ የለም፡፡ ይህም ከአላህ ዘንድ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ በመሠረቱ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተቃርኖ መኖሩ ያ መጽሐፍ ሁሉን አዋቂ ከሆነው አምላክ ዘንድ እንደልሆነ ቢያረጋግጥም ነገር ግን አንድ መጽሐፍ እርስ በእርሱ አለመቃረኑ ለመጽሐፉ መለኮታዊ ምንጭነት ማረጋገጫ ሊሆን እንደማይችልም መታወቅ አለበት፡፡ ብዙ እርስ በእርሳቸው የማይቃረኑ የልብ ወለድ መጽሐፍት በዓለም ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ተቃርኖ በውስጣቸው ያለመኖሩ እውነት እንዲሆኑ አያደርጋቸውም፡፡ ዑስማንን በመሳሰሉ ሰዎች የእርማት ሥራ የተሠራለት ቁርአንም ተቃርኖ በውስጡ ባይገኝ አስደናቂ አይሆንም፡፡ እርስ በእርሱ ስላልተቃረነም እንደ ፈጣሪ ቃል አንቀበለውም፡፡ ነገር ግን ቁርአን ውስጥ ተቃርኖ የለም የሚለው አባባል በገሃዱ ዓለም ሲፈተሽ የንግግርን ያህል ቀላል እንዳልሆነና ሙስሊሞች ጊዜ ወስደው ሊመለከቷቸው የሚገቡ ነጥቦች መኖራቸውን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ይህንንም ስንናገር ሙስሊም መዳጆቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላነሷቸው ክሶች አፀፋ ለመመለስ አይደለም፡፡ ቀጥሎ ለሚቀርቡት የመጽሐፋቸው ችግሮች ምላሽ ሊኖሯቸው አይችልም ከሚል አስተሳሰብ በመነሳትም አይደለም፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ቀላል እንደማይሆኑላቸው ብንገምትም ነገር ግን መልስ እንዳላቸው እንደሚያምኑ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እነርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለሚያነሱአቸው ጥያቄዎች ክርስቲያኖች በቂ ምላሽ እንዳላቸው ይገነዘቡ ዘንድ በፍፁም ቅንነት እንጠይቃለን፡፡ ሙስሊሞች ሁሉ ሆይ እኛ ክርስቲያኖች ትችቶቻችሁን በበጐ መልኩ ተቀብለን በማስተናገድ ለጥያቄዎቻችሁ በተገቢው መልኩ ምላሽ እንደምንሰጥ ሁሉ እናንተም ለእነዚህ በመጽሐፋችሁ ውስጥ ለሚገኙ ተቃርኖዎች ተገቢውን ምላሽ በቅንነት እንደምትሰጡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

1.     አጋሪ ሴቶችን (ከአላህ ውጪ ሌላ ነገር የሚያመልኩትን) ማግባት ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?

አልተፈቀደም- ቁርአን 2.221 “(በአላህ) አጋሪ የሆኑ ሴቶችን እስኪያምኑ ድረስ አታግቧቸው፡፡”

ተፈቅዷል- ቁርአን 5.5 “ከነዚያ ከናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም ዘማዊዎችና የሚስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትሆኑ ጥብቆች ሆናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቧቸው የተፈቀዱ ናቸው)”

ነገር ግን የመጽሐፉ ሰዎች (ክርስቲያኖችና አይሁዶች) አጋሪዎች እንደሆኑ ቁርአን በብዙ ስፍራዎች ላይ ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ክርስቲያኖች ኢየሱስን በማምለካቸው ሳቢያ አጋሪዎች እንደሆኑ ቁርአን 4.17፤ 5.72-73፤ 5.116 ላይ ተጽፏል፡፡ እንዲሁም አይሁዶች ዕዝራን የእግዚአብሔር ልጅ በማለት ስለሚጠሩት አጋሪዎች እንደሆኑ ቁርአን 9.20 ላይ ተጽፏል፡፡ ይህንን አይን ያወጣ ግጭት ለመረዳት የሚከተለውን ሲሎጂዝም ልብ ይበሉ፡-

      አጋሪ ሴቶችን ካላመኑ በስተቀር አታግቡ፡፡

      ክርስቲያኖችና አይሁዶች አጋሪዎች ናቸው

      ክርስቲያኖችና አይሁዶችን አግቡ፡፡

ይህ ማብራሪያ የማያስፈልገው ተቃረኖ ነው፡፡


2. ጋኔንና ሰው የተፈጠሩት ለምንድ ነው?

-  አላህን ሊገዙ ብቻ ቁርአን 52.56 “ጋኔንና ሰው ሊገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም”

-  ለገሃነም መሙያ ቁርአን 7.179 “ከጋኔንና ከሰው ብዙዎችን  ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡” እንዲሁም ቁርአን 23.13፤ 11.119 ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ እናገኛለን፡፡ በሁለቱ ጥቅሶች መካከል ያለውን ተቃርኖ በግልፅ ማየት ለማንም የሚያስቸግር አይደለም፡፡

3. ሰዎችን የሚያጠመው አላህ ወይንስ ሰይጣን?

አላህ - ቁርአን 7.186 “አላህ የሚያጠመውም ሰው ለርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡”
         ቁርአን 16.93 “አላህ በሻም ኖሮ አንዲት ህዝብ ባደረጋችሁ ነበር ግን የሚሻውን ሰው ያጠማል የሚሻውንም ሰው ያቀናል፡፡ ትሰሩት ከነበራችሁትም ሁሉ በእርግጥ ትጠየቃላችሁ፡፡”

ሰይጣን - ቁርአን 4.119-120 “በእርግጥም አጠማቸዋለሁ ከንቱም አስመኛቸዋለሁ… የማይፈፀመውን ተስፋ ይሰጣቸዋል ያስመኛቸዋልም፡፡ ሰይጣንም ለማታለል እንጂ አይቀጥራቸውም”
   ቁርአን 7.202 “ወንድሞቻቸውም (ሰይጣናት) ጥመትን ይጨምሩላቸዋል ከዚያም እነሱ አይገቱም”

   ሰይጣንም ራሱ “ጌታዬ ሆይ እኔን በማጥመምህ ይሁንብኝ” በማለት ለራሱ ጠማማነት አላህን ተጠያቂ ሲያደርግ በሱራ 15፡39 ላይ እናነባለን፡፡ እንዲሁም ሱራ 16፡93 ላይ እንደምናነበው አላህ ራሱ ሰዎችን አጣሟቸው የፈጠረ ሲሆን ነገር ግን “በስራችሁ እጠይቃችኋለሁ!” ብሎ ሲዝትባቸው እናያለን፡፡ ራሱ አጣሞ ከፈጠረ በኋላ ስለጠመማችሁ እጠይቃችኋለሁ ማለት በራሱ ትልቅ ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ለእኛ እስከሚገባን ድረስ ሰዎችን ማጥመም የጠማማው የዲያቢሎስ ሥራ እንጂ የፃድቁ የእግዚአብሔር ሥራ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡

4. አማላጆች አሉ ወይስ የሉም?

አሉ፡- “… መላእክትም ጌታቸውን እያመሰገኑ ያወድሳሉ፤ በምድርም ላለው ፍጡር ምህረትን ይለምናሉ…”  ቁርአን 42.5፣ እንዲሁም ቁርአን 33.43፤ 4.7 ይመልከቱ

የሉም፡- “…ከርሱ ሌላ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም አትገሰፁምን?” (ቁርአን 32.4)፣ በተጨማሪም የሚከተሉትን ተመልከቱ (ቁርአን 2.47-48፣ ቁርአን 2.122-123)

መላእክት በምድር ላለው ፍጡር ምህረትን የሚለምኑ ከሆነ ከአላህ ሌላ አማላጅ የላችሁም የሚለው ሀሳብ ከባድ ተቃርኖ ነው፡፡ ከአላህ ሌላ አማላጅ የላችሁም ማለትስ ምን ማለት ነው? አላህ ራሱ ከራሱ ምህረትን ይለምናል ማለት ነውን? ከሆነ አላህ በባህሪም በአካልም አንድ (ነጠላ) ነው ከሚለው የእስልምና አስተምህሮ ጋር እንዴት ይሄዳል? ሱራ 39.44 ላይ የሚገኘው ቃል አላህ አማላጅ እንደሆነ የሚናገረውን ሀሳብ ያጠናክራልና ያንብቡት፡፡

5. አላህ ያለሚስት ልጅ ሊኖረው ይችላል ወይስ አይችልም?

ይችላል፡- “አላህ ልጅን መያዝ በፈለገ ኖሮ ከሚፈጥረው ውስጥ የሚሻውን ይመርጥ ነበር ጥራት ተገባው፡፡” ቁርአን 39.4፡፡

አይችልም፡- “… ለርሱ ሚስት የሌለችው ሲሆን እንዴት ልጅ ይኖረዋል?” ቁርአን 6.101፡፡

በመጀመሪያው ጥቅስ ውስጥ አላህ ከፍጡራን መካከል የሚፈልገውን በመምረጥ (በምርጫ) ብቻ ልጅ መያዝ እንደሚችል ሲናገር ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ሚስት የሌለችው ሲሆን እንዴት ልጅ ይኖረዋል? በማለት የመጀመሪያውን ሀሳብ ያፈርሳል፡፡ በተጨማሪም በቁርአን 6 ላይ ያለው ሁለተኛው ጥቅስ በአላህ ሁሉን ቻይነት ላይ ከባድ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ምክንያቱም አላህ ያለሚስት ልጅ ሊኖረው የማይችል ከሆነ ሁሉን ቻይ አይደለም ማለት ነው፡፡

6. አላህ ብቸኛ ረዳት ወይስ ሌሎች ረዳቶችም አሉ?

ብቸኛ ረዳት፡- “አላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ህያው ያደርጋል ይገድላልም፤ ለናንተም ከርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም” ቁርአን 9.116፡፡

ሌሎች ረዳቶችም አሉ፡- “ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው…” ቁርአን 5.55 እንዲሁም ቁርአን 9.71፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “ረዳት” የሚለው ቃል በአረቢኛ “ዋሊ” ሲሆን ከዘጠና ዘጠኙ የአላህ መጠሪያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ እነዚህን መጠሪያዎች ደግሞ ለሌላ ፍጡር መስጠት በእስልምና የተውሂድ አስተምህሮ መሰረት ከባድ ኃጢአት ነው፡፡ ቁርአን 5.55 ላይ የሚገኘው ቃል ይህንን መጠሪያ ለሌሎች ከመስጠቱም በላይ በቁርአን 9.116 ላይ ካለው ከመጀመሪያው ጥቅስ ጋር በግልፅ ይቃረናል፡፡ በሌላም ስፍራ ላይ እንደዚሁ ሐዋርያት ራሳቸውን “የአላህ ረዳቶች” ብለው መጥራታቸውን እናነባለን ቁርአን 3.53፡፡ ታዲያ አላህ ብቸኛ “ዋሊ” ነው ወይስ አይደለም?

7.  የመላእክት ስግደት ለማን?

ለአላህ ብቻ፡- “እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት (መላእክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም ያወድሱታልም ለርሱ ብቻ ይሰግዳሉ፡፡” ቁርአን 7.206

ለሰው ሰግደዋል፡- “ለመላእክት ለአደም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ) ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ ኢብሊስ (ዲያቢሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ  ኮራም ከከሐዲዎቹም ሆነ፡፡” ቁርአን 2.34 በተጨማሪም ቁርአን 1.61፤ 15.30 አንብቡ፡፡

በመሰረቱ ስግደት የሚገባው ለጌታ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር መስገድ ያለበት ለፈጠረው አምላክ እንጂ ለሌላ ፍጡር መሆን አይገባም፡፡ ከዚህ ሀሳብ ጋር የማይስማማ ሙስሊም የሚኖር አይመስለንም፡፡ ሙስሊሞች ቀደም ሲል በተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት እንደሌለ ሊያስረዱን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እውነተኛው አምላክ መላእክት ለሰው ይሰግዱ ዘንድ ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት አንዱ ፍጡር ለሌላው ፍጡር ይሰግድ ዘንድ እንዳስተማረ የሚናገረውን ጥቅስ ከአጠቃላይ የቁርኣንና የእስልምና ትምህርት ጋር እንዴት ያስታርቁት ይሆን?

8. የአላህ ቃል ይለወጣል ወይስ አይለወጥም?

ይለወጣል፡- “ከአንቀፅ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ቢጤዋን እናመጣለን፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መሆኑን አታውቅምን?” ቁርአን 2.106

“በአንቀፅ ስፍራ አንቀፅን በለወጥን ጊዜ አላህ የሚያወርደውን ነገር አዋቂ ነው፡፡

አንተ ቀጣፊ እንጂ ሌላ አይደለህም ይላሉ በውነቱ አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡” ቁርአን 13.39

አይለወጥም፡- “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም፡፡” ቁርአን 18.27 “ለአላህ ድንጋጌ ፈፅሞ መለወጥን አታገኝም፡፡” ቁርአን 33.26 “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም፡፡” ቁርአን 10.64

እንዲሁም ቁርአን 6.115 እና 6.34 ያንብቡ፡፡

በአማርኛው ቁርአን የተወሰኑ ገፆች ላይ አንዱ አንቀፅ (ጥቅስ) በሌላው መሻሩን የሚያሳስቡ የተለያዩ የግርጌ ማስታወሻዎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ገፅ 18, 26, 53, 55, 123, 297 ይመልከቱ፡፡

ይህ አይነቱን የቁርአን እርስ በእርስ መሻሻር ሙስሊም ምሁራን በእንግሊዘኛ ‘Abrogation’ በማለት ይጠሩታል፡፡ ሁኔታን ተመልክቶ ትላንት የተናገረውን ቃል የሚያጥፍና የሚለዋውጥ ደካማ የሆነው የሰው ልጅ እንጂ እውነተኛው አምላክ እንዴት ሊሆን ይችላል? እንኳንስ ሁሉን አዋቂ የሆነው ሀያሉ ጌታ ይቅርና ከሰው ልጆች መካከል ጨዋ የሚባለው እንኳ ትላንት ለተናገረው ቃል ታማኝ የሚሆን ነው፡፡

9. በገሃነም ውስጥ የተጣሉ ሰዎች ምግብ አንዱ ብቻ ወይስ ሁሉም?

ዶሪዕ የሚባል ዛፍ ብቻ፡-
“ለነሱ ዶሪዕ ከሚባል (እሾሃም) ዛፍ እንጂ ሌላ ምግብ የላቸውም፡፡” ቁርአን 86.6

የዘቁም ዛፍ የሚባል፡- “በመስተንግዶ ይህ ይበልጣልን ወይስ የዘቁም ዛፍ?... እርሷ በገሃነም አዘቅት ውስጥ የምትወጣ ዛፍ ናት፡፡ እንቡጧ ልክ የሰይጣናት ራሶች ይመስላል፡፡ እነርሱም ከርሷ በይዎች ናቸው…”  ቁርአን 37.62-68 እንዲሁም ቁርአን 56.52 ያንብቡ

የቁስል እጣቢ ብቻ፡- “ምግብም ከእሳት ሰዎች ቁስል እጣቢ (እዥ) በስተቀር የለውም” ቁርአን 69፡36

በገሃነም የተጣለ ሰው ምግብ ዶሪዕ ብቻ? የቁስል እጣቢ ብቻ? ወይስ የዘቁም ዛፍ? እንዲሁም ቁርአን በገሃነም የተጣለ ሰው የፈላ ውሃ እንደሚጠጣ ይናገራል፡፡ ቁርአን 56፡54-56
 
10.  መሐመድ ቢሳሳት የሚጐዳው ማነው?

እስኪ የሚከተለውን የቁርአን ጥቅስ በአንክሮ ያጢኑ፡-

ቁርአን 34.50 “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡”

ሙሐመድ “እኔ ያመንኩትን እመኑ ተከተሉኝ” እያለ መለስ ብሎ ደግሞ “ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው” ማለቱ በእጅጉ ያስገርማል፡፡ ይህ ጥቅስ በአረብኛ እና በእንግሊዘኛ የቁርኣን መጽሐፍቶች ይበልጥ ግልፅ ሆኖ ይነበባል፡፡ ሐሳቡም መሐመድ ትክክል ካልሆነ (ከተሳሳተ) የሚጐዳው እርሱ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡  ሙስሊሞች ከአለባበስ ጀምሮ እሰከ ጢም አቆራረጥ ድረስ መሐመድን መምሰል ወሳኝ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ መሐመድ ልክ ከሆነ የእርሱን ትምህርት የተቀበሉና የተከተሉት ሰዎች ሊድኑ ይችላሉ፡፡ እርሱ ትክክል ካልሆነ ግን ይጠፋሉ፡፡ ምክንያቱም ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ አስተማሪዎችን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ይጠፋሉና፡፡ መሐመድ ትክክለኛ ነቢይ ሆነም አልሆነም ይህ አይነቱ ንግግር ስህተት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ቢሳሳት የሚጐዳው እርሱን የተከተለ ሰው ሁሉ እንጂ እርሱ ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ ያየናቸው የቁርአን እርስ በእርስ ግጭቶች ወይንም ቅራኔዎች እጅግ በጣም ብዙ ከሆኑት መካከል በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ቅራኔዎች ለአንባቢዎች በተከታታይ እናቀርባለን፡፡ ይህንን የምናደርግበትም ዓላማ አንባዎች ስለ ቁርአን ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ነው፡፡

ስለ እምነቶች በተለይም እንከተለዋለን ስለምንለው እምነት እውነቱን መረዳት እጅግ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ እናምናለን ምክንያቱም እምነታችን የዚህን ዓለም ኑሮ ብቻ ሳይሆን ዘላለምን የት እንደምናሳልፍ  ይወስነዋልና፡፡

ለዘላለም ሕይወታችን ይጠቅመናል ብለን የምንከተለው እምነት የተመሰረተበት መሰረት እውነት መሆኑ ደግሞ ትክክል ወይንም ስህተት ለመሆኑ ዋና ጠቋሚ ነው፡፡ ስለዚህም እነዚህ የቁርአን እርስ በእርስ ቅራኔዎች በራሳቸው የሚናገሩትን ነገር አንባቢዎች ቆም ብለው እንዲያስቡበትና ስለ ዘላለማዊ ሕይወታቸው ምን ማድረግ እንደሚገባቸው እራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ለሕይወት መመሪያ ይሆናል ተብሎ በሚታሰብ መጽሐፍ ውስጥ የእርስ በእርስ ቅራኔ ስለምን ተገኘ? በቁርአን ውስጥ የሚገኙ በርካታ የእርስ በእርስ ቅራኔዎች የሚያስከትሉት ጥያቄ ምንድነው? በቁርአን ውስጥ ላሉት የእርስ በእርስ ቅራኔዎች ሎጂካል መልስ መስጠትና የአንባቢን ጥያቄ ማርካትና መመለስ ይቻላልን? እነዚህና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንባቢዎች እንዲያስቡባቸው እንተውላቸዋለን፡፡

ይሁን እንጂ በቁርአን ውስጥ ያሉት ቅራኔዎች ነቢይ ነኝ በማለት ከተናገረውና መገለጥ ነው ብሎ ከተጻፈው ጽሑፍ እንዲሁም ልኮኛል በማለት በተናገረው አምላክ ላይ ሰዎች ትልቅ ጥርጥር እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡፡

መፍትሔው ምንድነው? መፍትሔው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መምጣትና ክፍት በሆነ አዕምሮ ማንበብ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ቅራኔ የሌለው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን የሚለውጥ መልእክት አለው፡፡ አንባቢዎች ሆይ መጽሐፍ ቅዱስን አግኝታችሁ እንድታነቡና ነፍሳችሁን በቃሉ እንድትመግቡ እንጋብዛችኋለን፣ እግዚአብሔር በቃሉ የሚናገራችሁ ንስሐ በመግባት እርሱ ባዘጋጀው የመዳን መንገድ ውስጥ ገብታችሁ የዘላለምን ሕይወት እርግጠኝነት እንድታገኙ ነው ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ