ዘመናዊ ሳይንስ በቁርአን ውስጥ ሊገኝ ይችላልን?
በAndy Bannister
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
እንደ soc.religion.islam ዓይነት የዜና ቡድኖችና በሌሎችም አካባቢዎች በጣም ብዙ ጊዜ ልዩ የሆነ አንድ ነገር ብቅ ይላል፡፡ ይህም በቁርአን ገፆች ውስጥ ዘመናዊ ሳይንስ ይገኛል የሚል ማሳሰቢያን በተመለከተ ነው፡፡ ከኮሜቶች እስከ አስትሮኖሚ፣ ከኢምቢሪዮሎጂ እስከ ጂኦሎጂ እነዚህ ሁሉ በተለያዩ የቁርአን ምዕራፎች ውስጥ ይገኛሉ ተብለው እየቀረቡ ናቸው፡፡ ከዚያም ቀጥሎ እነዚህን ሳይንሶች መሐመድ ሊያውቃቸው የማይችል ስለነበር ቁርአን መሆን ያለበት መለኮታዊ ነው የሚል ሐሳብ ደግሞ እንደማስረጃ ይቀርባል፡፡
የተለያዩ የሳይንስ ነጥቦችን ይዞ ይህንን የሙስሊሞችን አቅርቦት የሚነቅፍ ክርክር ብዙውን ጊዜ የቀረበው አስደናቂ በሆነው በAndrew Vargo ስራ ላይ ነው (ይህንንም ስራ ወደፊት አዘጋጆቹ ለማቅረብ ይጥራሉ)፡፡ ይህንን ማድረግ በጣም ቀላል ቢሆንም ደጋግሞ መስራቱ ግን አሰልቺ ነው፡፡ ስለዚህም በዚች አጭር ጽሑፍ ውስጥ እኔ የሞከርኩት “በቁርአን ውስጥ ዘመናዊ ሳይንስ አለ” የሚባለውን ፅንሰ ሐሳብ እራሱን ለማፍረስ ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ ሳይንስ አለ የሚለው ክርክር እራሱ መሰረታዊ የሆነ የሎጂክ ስህተት ያለበት ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ወረቀት ላይ ያሉት ስድስት ነጥቦች በቁርአን ውስጥ አሉ የሚባሉት የኢምብርዮሎጂ፣ የጂኦሎጂ ወይንም ሌሎች የሳይንስ ማገናዘቢያዎች ሁሉ ትክክል አለመሆናቸውን ያሳያሉ ብዬ አምናለሁኝ፡፡
ይህ ጽሑፍ የተነሳሳው ስለ ወንዞችና ባህሮች ከsoc.religion.islam የዜና ቡድኖች ጋር ከተደረገው ክርክር በኋላ ነው ስለዚህም ያንን በተመለከተ ማገናዘቢያዎች ይገኛሉ፡፡
ለማንኛውም ግን “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለው ሐሳብ ውስጥ ያሉት ስድስቱ መሰረታዊ ስህተቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
እኔ ተስፋ የማደርገው ይህንን ጽሑፍ ሰዎች ጠቃሚ ሆኖ እንዲያገኙት ነው፡፡ እኔ አስደናቂም አበረታቺም ሆኖ ያገኘሁት ነገር አንዳንድ ሙስሊሞች የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡ ብዙ ሙስሊሞች እኔ ካልኩት ጋር የሚስማሙና ቁርአንን (እስልምናን) ለማሰራጨት ይህንን ሐሳብ ለመጠቀም ከሚሞክሩት ጓደኞቻቸው ጋር የማይስማሙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌም አብዱልራህማን ሎማክስ ከዚህ በታች ከቀረቡት ውስጥ ስለ ነጥብ 4 የሚከተለውን ጽፏል፡- “በቁርአን ውስጥ ሳይንስ አለ የሚለውን ሐሳብ ሊቃውንቱ በአጠቃላይ የማይቀበሉበት ምክንያት በእርግጥ ይህ ነው” በማለት ተናግሮ በመደምደሚያው ላይ የኔን ጽሑፍ አስመልክቶ ደግሞ የሚከተለውን “በመሰረቱ አንዲ ትክክል ነው” በማለት ተናግሯል፡፡
ነጥብ አንድ: ይህን መከራከሪያ የሚከተሉት ሁሉ ለተለዋጭ አተረጓጎም ምንም የሚሰጡት ክፍተት የለም፡
አንድ የተወሰነ የቁርአን ቁጥር የሚለውን በተመለከተ ብዙውን ጊዜ ሙስሊሞች ተለዋዋጭ ትርጉሞች አሏቸው፣ ይህም የቁርአን ዋነኛው ባህርይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ በተመለከተ ምንም ችግር አይኖርም ምክንያቱም አንድ ቁጥር የተገለጠበትን ትክክለኛውን ታሪካዊ ዓውድ በተለይ ካላወቅን በስተቀር ብዙውን ጊዜ ትርጉም አስቸጋሪ ጉዳይ ይሆናልና ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል በቁርአን 18 ውስጥ የተገለጠውን ዱአልቃርናይን ውሰዱ፤ በቁርአን ውስጥ ያለው ይህ ምስጢራዊ ተጓዥ ማን መሆኑን በተመለከተ በሙስሊሞች መካከል ክፍፍል አምጥቷል፡፡ አንዳንዶች (ለምሳሌ ዩሱፍ አሊ) የሚያምነው እርሱ ታላቁ አሌክሳንደር ነው በማለት ነው፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህ ሐሳብ ጋር አይስማሙም እናም ሌላ ፅንሰ ሐሳብ አላቸው፣ ለምሳሌም ያህል እርሱ ታላቁ ቂሮስ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህንንም በተመለከተ ጤናማ ክርክር ለማድረግ እጅግ በጣም ብዙ ሰፊ ነገር በዚህ ውስጥ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ “ዘመናዊው ሳይንስ ቁርአንን ይደግፋል” በማለት የሚሰብኩት እነዚያ ደግሞ የሚያቀርቡትን ሐሳብ በተመለከተ አንድ ጥቅስ በሚለው ሐሳብ ላይ እና በራሳቸው ትርጉምም ላይ እንኳን አይመሰረቱም፡፡ በእርግጥ የእነርሱን አቋም መጥቀስ ብቻ የሚሻል ይመስላል እርሱም የሚለው፡ “ቁርአን ዘመናዊ ሳይንስ ይገኝበታል”፤ ብሎ ማመንና፤ ይህም “እርሱ ከአላህ የመጣ እንደሆነ ያሳያል” የሚለውን አቋማቸውን ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቁርአን ውስጥ ያለ አንድም ጥቅስ እንኳን ቀጥተኛ ሳይንስ ያለው ሆኖ እስከ አሁን ድረስ በፍፁም አልተገኘም (ይህንን በተመለከተ የሚቀጥለውን ነጥብ 2 ላይ ብዙ ተብሏልና ተመልከቱ)፡፡
ለምሳሌም ቁርአን 25.53 እንደገና ተመልከቱ፣ soc.religion.islam የሚባሉት የዜና ቡድኖች፤ “በቁርአን ውስጥ ዘመናዊ ሳይንስ አለ” የሚለውን የተለየ አካሄድ እንዲያመጡ ያስጀመራቸው ይህ ጥቅስ ነበር፡፡ ጥቅሱም እንደሚከተለው ይላል፡
“እርሱም ያ ሁለቱን ባህሮች አጎራብቶ የለቀቀ ነው ይህ ጥምን የሚቆርጥ ጣፋጭ ነው ይህም የሚመረግግ ጨው ነው በመካከላቸውም (ከመቀላቀል) መለያንና የተከለለን ክልል ያደረገ ነው” ቁርአን 25.53፡፡ (የአማርኛው ትርጉም)፡፡
አሁን እኔ እከራከረው የነበረው ሙስሊም (እንዲሁም በሌሎች ብዙዎች ይደገፍ የነበረው) ይከራከር የነበረውና ያቀረበው ሐሳብ የሚከተለውን ነው፡-
“ከዚህ በላይ ያለው የቁርአን ጥቅስ በግልጥ የሚጠቅሰው ትልልቅ ወንዞች ከትልልቅ ባህሮችና ውቅያኖሶች ጋር ስለሚገናኙበት ሁኔታ ነው፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ወንዙ ከባህሩ ውሃ ጋር ሳይደባለቅ ማለትም ሁለቱ ውሃዎች ሳይደባለቁ ለብዙ ማይልሶች ይጓዛል፡፡ ይህም በአሁኑ ጊዜ ባሉ ሳይንቲስቶች በጣም የታወቀ ክስተት ነው፣ እንዲሁም ደግሞ ቁርአን በግልፅና በማይካድ ሁኔታ የጠቆመው ለዚያ ያለውን ምክንያት ነው፡፡ በዘመናዊ ሳይንሳዊ ቃላት (አነጋገር) የአንዱን ጣፍጭነት እና የሌላውን ጨውነት በማለት ነው፡፡ ማለትም በሁለቱ ውሃዎች መካከል ያለውን (የስበት) ግራቪቲ ልዩነቶች ነው፣ ይህ ደግሞ በዘመናዊ ሳይንቲስቶችም የተሰጠው መግለጫ ነው” (Suleiman, in thread "Scientific facts and Qur’an", soc.religion.islam, 4-Nov-99;)
ይሁን እንጂ የተለያዩ የእንግሊዝኛ የቁርአን ትርጉሞችን ስትመለከቱና ስታወዳድሩ ማስተዋል የምትጀምሩት ጥቅሱ ስለ ወንዞች ምንም ነገርን አይናገርም፡፡ የአረብኛውን ጥቅስ ስንመለከት የሚናገረው ስለ ውሃዎች ክምችት ብቻ ነው (ይህንን በመጠቆሜም ያመሰገነኝ አንድ ሙስሊም አለ)፡፡ (የአማርኛውም ትርጉም ሁለቱን ባህሮች እንጂ ወንዞችን አይጠቅስም)፡፡ ይህን በተመለከተ ያሉትን የሚከተሉትን ሦስት የእንግሊዝኛ ትርጉሞች አስተውሉ፡-
ዩሱፋሊ፡ እርሱ ነው ሁለቱን የሚፈስሱ ውሃዎች የለቀቃቸው እርሱ ነው፡፡ አንዱ ጣፋጭ ሌላው ደግሞ ጨውና የሚመርር ናቸው፣ ነገር ግን እርሱ በመካከላቸው መለያን አደረገ፤ መክፈያ፤ ለማለፍ የተከለከለ መለያን አደረገ፡፡
ፒክታል፡ ለሁለቱ ባህሮች ነፃነትን የሰጠው እርሱ ነው (ምንም እንኳን ቢገናኙም) አንዱ ጣፋጭ የሚጥም ሌላው ደግሞ ጨዋማ መራር እና በእነርሱ መካከል መከለያን አስቀመጠ እንዲሁም በመካከላቸው የሚከልክን ማገጃ አደረገ፡፡
ሻኪር፡ እርሱ ነው ሁለቱን ባህሮች በነፃነት እንዲፈስሱ ያደረገው አንዱ ጣፋጭና ጥማትን በጥፍጥናው የሚያረካ ሌላው ደግሞ ጨዋማ በጨውነቱ የሚያቃጥል ነው በእነርሱም መካከል እርሱ መከለያንና የማይታለፍን ማገጃ አደረገ፡፡
እንግዲህ “ዘመናዊ ሳይንሳዊ” የሚባለው የትርጉም እንዲሰራ ከተፈለገ አንድ ሰው አፅንዖት ማድረግ ያለበት ነገር እነዚህ ሁለቱ ባህሮች ወይንም የውሃ አካላት (ሁለቱም) “ባህሮች አይደሉም”፤ ነገር ግን አንደኛው ወንዝ ነው በማለት መሆን አለበት፡፡ አረብኛው ግን ያንን ልዩነት አያደርግም (የአማርኛውም ባህሮች ብቻ ነው የሚለው)፡፡ ይህ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድነው? ምክንያቱም በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ዘመናዊ ሳይንስን ለማግኘት ሱለይማንና መሰሎቹ ማጠንከር ያለባቸው አንዱ የውሃ አካል ወንዝ ነው (ፍሬሽ ውሃ) እንዲሁም ሌላው ደግሞ ባህር ነው (የጨው ውሃ) በማለት ብቻ ሲሆን ነው፡፡ ከዚያም እነርሱ ማስገባት ያለባቸው ሐሳብ የፈሳሽ ውሃ የወንዝ ውሃ በተለምዶ ፍሬሽ ውሃ የሚባለው በባህር ውስጥ ሲፈስስ አይደባለቅም የሚለውንም ሐሳብ ነው፡፡ አሁን ግን እኔ የምለውንም ሆነ ሱለማይንና ጓደኞቹ የሚሉትን ነገር ማለትም ሁለቱ ውሃዎች ይደባለቃሉ ወይንስ አይደባለቁም የሚለውን ወደ ጎን ተወት አድርገን በጣም መሰረታዊ የሆነ ጉዳይ እንዳለን መገንዘብ አለብን፡፡ አረብኛው አንዱ ወንዝ ነው የማይል ከሆነ ይህ ክፍል በጣም ቀላል የሆነ ትርጉም አለው ማለት ነው፡-
1. የመጀመሪያው ባህር ወይንም “ትልቅ ውሃ” ወይንም በአረብኛ “ባህር” በዚህ ቦታ ላይ ያለው ቀይ ባህር ነው (ለመካና ለመዲና ቅርብ የሆነው)፤ እርሱም መሐመድ የሚያውቀውና የጨው ውሃ ነው፡፡
2. ሁለተኛው ባህር “ትልቅ ውሃ” ወይንም “ባህር” በአረብኛው የተጠቀሰው ማንኛውም የአካባቢው ትልቅ ውሃ ሊሆን ይችላል ጨዋማ ያልሆነው (ለዚህም ሊመረጡ የሚችሉ እጅግ በጣም ብዙ ዖሲሶች በአረቢያ ውስጥ ይገኛሉ)፡፡
3. እነዚህ ሁለቱ ባህሮች ወይንም “የውሃ አካላት” ወይንም “ባህሮች” በአረብኛ አንዳቸው ከሌላቸው በምድር የተለያዩ ናቸው፣ ይህ ምድር ደግሞ ሊቋረጥ የማይቻለው እገዳ ነው ማለት ነው፡፡
4. ስለዚህም ቁርአን 25.53 መሐመድ እንዳየው ከሆነ ጨዋማውን ውሃ ጨዋማ ካልሆነው ውሃ በአላህ በሚገባ እንዲለያዩ መደረጋቸውን እንደ ድንቅ ተዓምር አድርጎ የገለጠበት ክፍል ነበር፡፡
ሱለይማንና ሌሎች ጓደኞቹ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ዘመናዊ ሳይንስ ተዓምር” አለበት ከሚሉት ይልቅ ከዚህ በላይ የተሰጠው ትርጉም በጣም ብዙ የሆኑ ጠቀሜታዎች አሉት ጠቀሜታዎቹም፡-
1. ሱለማይን የተናገረው መሐመድ ምናልባትም ወንዝ ወደ ባህር ውስጥ ሲፈስ አይቶ አያውቅም ይሆናል (እርሱ የኖረው ከወንዞችና ከባህሮች ብዙ መቶ ማይልሶችን ርቆ ነበር፣ ይህ ሱለማይን በመጀመሪያ በሕዳር 4 1999 በረጨው ጽሑፍ መሰረት ነው)፡፡ በዚህ አረፍተ ነገር አማካኝነት ሱለማይን ትክክል ቢሆን ኖሮ፤ እኔ ከዚህ በላይ ከሰጠሁት ትርጉም ጋር ይስማማ ነበር፣ በመሐመድ አዕምሮ ውስጥ ጨዋማ ያልሆነ እና ጨዋማ ውሃ አይገናኙም፡፡ (እንዳይገናኙ በመካከላቸው ባለው ምድር ተከልለዋልና)፡፡
2. ይህም ማለት ቁርአን 25.53 ጥቅሱ በተጻፈበት ላለው ጊዜ (600 ዓ.ም) እና አሁንም፣ (ትርጉም አለው ማለት ነው)፤ ማለትም በአሁኑ ዘመን ያሉ ሙስሊሞች አንብበው ሊገነዘቡት እንደሚችሉት በመጀመሪያ ያነበቡት ሙስሊሞችም ይረዱት ነበር እንዲሁም ስለዚህ የእግዚአብሔር ስጦታ እርሱን ያመሰግኑት ነበር፡፡ ካልሆነም ሌላው (አማራጩ) ትርጉም ማለትም (”ዘመናዊ ሳይንስ በቁርአን አለ”) የሚጠይቀው ይሆናል፡፡ ስለዚህም “በዘመናዊ ሳይንስ በቁርአን አለ” ትርጉም መሰረት ይህ ጥቅስ ለ1300 ዓመታት ያህል ትርጉም ያልነበረው ሆኖ ይቀራል ማለት ነው፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው የዘመናዊ ሳይንስ ዕድልን ያገኘነው እኛ ምናልባትም እስከገባንና እስከተረጎምነው ድረስ ማለት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ቁርአን በሁሉም ጊዜ ለነበሩት ሰዎችና ለሁሉም ሰዎች ምንም ጥቅም የሌለው ነበር ማለት ነው፡፡
3. ከዚህም በላይ መሐመድ ለምን ቁርአን 25.53 እንደጻፈው ይገልፃል፡፡ የወንዞች ወይንም ባህሮች እንዲሁም ደግሞ መደባለቅ ወይንም አለመደባለቆች ፅንሰ ሐሳብ ምንም ግንዛቤ ባይኖረውም እንኳን እርሱ የጨዋማ ያልሆነውን ውሃ ጠቀሜታ ተገንዝቧል፡፡ እንዲሁም ደግሞ የጨዋማ ያልሆነው (የሚጠጣው) ውሃ መገኘትን መሐመድ ያየበትን ምክንያትም በትክክል የምንረዳው ነገር ነው፡፡ የሚጠጣውን ውሃ ከማይጠጣው የጨው ውሃ መለየት የአላህ ስጦታ አንዱ ምሳሌ ነው ስለዚህም ይህንን መጥቀስ ተገቢ ነው በማለት ነው፡፡
ቁርአን 25.53 ለመጠቀምና “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ይደግፋል” የሚለውን አቋም ለመደገፍ እንዲቻል ይህ የኋለኛው እኔ የሰጠሁት የቁርአን ትርጉም መኮነን አለበት፡፡ ይህም የበፊቱን ትርጉም ማለትም የእነ ሱለይማንን ትርጉም ለመደገፍ እንዲቻል ነው፡፡ ከተደረገ ደግሞ የበፊቱን ሐሳብ ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ምንም እውነተኛ ማስረጃ ሳይቀርብለት ሲሆን፣ መወሰድም ያለበት የግድ እውነት መሆን አለበት ተብሎ ነው! ምክንያቱም ተዓምር ነውና! (ማስታዎሻ፡ የሱለይማን ትርጉም ቁርአን “ሳይንሳዊ ተዓምር” እንዳለው ምንም የሚያሳየው ነገር የለውም በቀላሉ የምናየው የእርሱ ትርጉም አንድ ልዩ ነገር ብቻ መባሉን ነው)፡፡
ነጥብ ሁለት፡ ሐሳቡ እራሱ አላህን ደካማ ያደርገዋል፡
አላህ ቁርአንን ለማረጋገጥ ሳይንስን የሚጠቀም ቢሆን ኖሮ፣ ታዲያ ያንን ካደረገ ያንን ሐሳብ ከሚደግፉት ሰዎች የብልጣ ብልጥነት ትርጉም ላይ ባልተመሰረተ መንገድ ለምን አላደረገውም ነበር? ይልቁንስ አላህ ምንም የማያከራክር ሊያደርገው አይችል ነበር እንዴ? ለምሳሌም ያህል ቴሌቪዥንን እንውሰድና አላህ ለመሐመድ እንደሚከተለው አለው እንበል፡ “ተናገር፡- ሰዎች በሚኖሩበት ቤታቸው ማዕዘን ጥግ በሚቀመጡ ትንንሽ ሳጥኖች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ምስሎችን ይመለከታሉ”፡፡ ወይንም ደግሞ የጨረቃ ላይ የተደረገውን ማረፍ በተመለከተ፡ “ተናር፡- (እንዲህ በላቸው)፡ ኦ! ሰዎች በጨረቃ ፊት ላይ ይጓዛሉ እንዲሁም ባንዲራን በላዩ ላይ ይተክላሉ”፡፡ እነዚህ ላይ ታያላችሁን? እንደዚህ ዓይነት ጥቅሶች አሁን ከምናየው ሁኔታ (ማለትም ቁርአን 25.53 ላይ ካለው ሁኔታ) በተቃረነ መልኩ ምንም ዓይነት መከራከሪያ አይኖራቸውም ነበር፡፡
ስለዚህም፡- ሀ. የነዚህ የተዓምር ጥቅሶች በሆነ መንገድ የተጠመዘዘ ትርጉም ይዘውና፤ ለ. እነርሱን በተረጎሟቸው ሰዎች አማካኝነት የሚሰጠው የከረረ አባባል ማለትም የእነርሱ ብቻ፣ የእነርሱ ትርጉም ብቻ ነው ትክክለኛው ተብሎ መወሰድ አለበት ማለታቸው (ይህም ከ1000 ዓመታት በፊት የነበሩት የሙስሊም ሊቃውንት ተርጓሚዎች የሰጡትን ትርጉም በመዝጋት ነው) በጭራሽ አይኖርም ነበር፡፡
ቁርአን ስለአንድ ጉዳይ ሲናገር እጅግ በጣም ግልጥ ሆኖ እንደሆነ በሌላም ቦታ ላይ ታያላችሁ፤ ለምሳሌም ያህል ቁርአን 3.2 ተመልከቱ፡
“አላህ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም (እሱ) ሕያው ሁሉን ነገር አስተናባሪ ነው” (የአማርኛው ትርጉም)፡፡
ይህ ጥቅስ የሚናገረው ብቸኛ አምላክ፤ የሚኖር፣ እራሱን የቻለ እና ሕያው የሆነው አላህ መሆኑን በተመለከተ ማንም ሰው ሊከራከር አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሚለው ነገር ምን እንደሆነ በጣም ግልጥ ነውና፡፡ ሙስሊሞች እንደሚናገሩት በቁርአን ውስጥ “ሳይንሳዊ ተዓምር” ካለ፣ ሊሆን የሚችለው በመለኮት የተጻፈ ለመሆኑ አስደናቂ ማስረጃ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሚባለው ተዓምር የተቀበረ (የተሰወረ) ነው፣ ማለትም እርሱን ለማግኘትና ለማውጣት ብልሃት የተሞላው አተረጓጎምን የሚፈልግ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ይህ አባባል ምንም የሚጨምረው ነገር የለውም፣ ይኖረዋልን? አላህ በቁርአን ውስጥ ተዓምር እንዲኖር አቅዶ ቢሆን ኖሮ እርሱ በግልጥ ሊጻፍ ያስፈልገው ነበር፡፡
ነጥብ ሦስት፡ ሐሳቡ ዘመናዊ የክርክሩ ዘይቤ ነው
“ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ይደግፋል” የሚለውን ሐሳብ በጣም አስገራሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት የነበረ የሙስሊሞች ሊቅ ይህንን ሐሳብ እንደማስረጃ እንዳቀረበው አንድ ሰው በማስረጃ አስደግፎ ሊያሳየን ይችላልን? ወይንም ከሁለት መቶ ዓመታት በፊትም እንኳን ከነበሩት ውስጥ? ወይንም ከአንድ መቶ ዓመታት በፊትም እንኳን? መልሱ፡ ምናልባት አይኖርም ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ይህ ሐሳብ ዘመናዊ የክርክር መንገድ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ሳይንስ የቅርብ ጊዜ ወይንም በቅርብ የመጣ ነገር አይደለም፣ ነገር ግን ይህ የመከራከሪያ ሐሳብ ግን በጣም የቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ለምን ይሆን? ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሰዎች ቁርአንን በጭፍንነት ከመቀበል ይልቅ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንደጀመሩ ሙስሊሞች የተገነዘቡት አሁን በጣም በቅርብ ጊዜ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም “ይህ አዲስ የክርክር ሐሳብ የተነሳሳው ቁርአን በመለኮት የተጻፈ መሆኑን ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን በጣም እየጨመረ ስለመጣ ነው፣ እስልምና ወደ ምዕራቡ ዓለም እየገባ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፣ ለምዕራቡ ዓለም አመለካከት የሚስማሙ፣ ለሳይንስ አቤቱታ ያቀረቡ ማስረጃዎችን፣ በመፈለግ ለማቅረብም ሲባል ጭምር ነው ፡፡”
አንባቢዎች ሆይ! የሚያስገርም ሐሳብ ይኸውላችሁ፡ “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን እያረጋገጠ” እያለ፣ የሙስሊሞች ክርክር የሚሆነው እንደሚከተለው ነው፡- “ዘመናዊው ክርክር እራሱን በራሱ ስህተት መሆኑን አያረጋግጥም” በማለት አስበው ወይንም ገምተው ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የመከራከሪያ መንገድ ለመጠቀም የሚፈልጉት ሙስሊሞች ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት መከራከሪያ በጣም አስገራሚ የሆነ ችግር አስነስቶባቸዋል፡፡ ችግሩ ደግሞ የሚከተለው ነው፣ እነርሱ በጣም ካልተጠነቀቁ ቁርአንን በአንድ ዘመን (የጊዜ ሁኔታ) ላይ ብቻ አስረው ያስቀሩታል ማለት ነው፡፡ ታያላችሁን አላህ ሳይንስን በቁርአን ውስጥ እንደመልክት አቅዶ ቢሆን ኖሮ፤ ቀጥሎ የሚገመተው ነገር ከአሁን አንድ መቶ ዓመት በኋላ ሙስሊሞች “ዘመናዊ” ሳይንስን በቀጣይነት ማግኘት መቻል አለባቸው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሳይንስ ያድጋል፡፡ ስለዚህም የሚከተሉትን ነገሮች አስተውሉ፡-
- ቁርአን የያዘው 6,400 የሚሆኑ ጥቅሶችን ነው፡፡
- ለክርክር ያህል እንበልና 10% የሚሆኑት እነዚህ ጥቅሶች በቅልጥፍና ሊተረጎሙ ችለው “ሳይንስ” እንዳለቸው ሆነው ቢገኙ፡፡
- ስለዚህም ለእኛ ምንጭ የሚሆኑ 640 (ሳይንሳዊ) ጥቅሶች ከቁርአን ውስጥ ይኖሩናል ማለት ነው፡፡
አሁን “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለው ሐሳብ ባላፉት 30 ዓመታት ውስጥ በጣም ታዋቂ እየሆነ እንደመጣው ሁሉ ብዙ የቁርአን ጥቅሶች እጅግ በጣም ብዙ በሆነ ሁኔታ እየተጠቀሱ ነው፡፡ ስለዚህም እንደዚህ እናስብ 20 የሚሆኑ አዳዲስ ጥቅሶች በየዓመቱ ሳይንስ እንዳላቸው ቢቀርቡ፡፡ ማለትም (የ30 ዓመት ጊዜ ተሰጥቶ) 90 በመቶ የሚሆኑት ጥቅሶች አግልግሎት ላይ ውለው አልቀዋል፡፡ ስለዚህም አምስት ዓመት ባላነሰ ጊዜ ውስጥ “ሳይንሳዊ” የሆነ የምንጭ ማስረጃ የሚሆነን ምንም ነገር አይኖረንም ማለት ነው፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ታያላችሁን? ከአስር ዓመታት በኋላ ወደ ኋላ ተመልሰን ስንመለከት በሙስሊሞች ታሪክ ውስጥ ከ700 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ውስጥ፤ ሰዎች የሚያዩት ቁርአን ለዘመናዊ ሳይንስ ተናግሯል የሚባለው ከ1970 - 2002 ድረስ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚያም ቁርአን ስለ ጉዳዩ መናገር ያቆማል፣ መገለጡም ምንም “ሳይንሳዊ” ምንጭ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ይህ እውነታ የሚናገረን ነገር ምንድነው? “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያስረዳል” የሚለው አነጋገር አንደኛ፡ ዘመናዊ ክርክር ብቻ ነው፣ ሁለተኛ፡ እርሱም የተወሰነው በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ ነው፤ ሦስተኛ፡ እርሱም እራሱን በራሱ ብዙ ሳይቆይ አቃጥሎ ያጠፋል ማለት ነው፤ ምክንያቱም ለዚህ ምንጭ የሚሆኑት ነገሮች ያልቃሉና ነው፡፡
ነጥብ አራት፡ በመጨረሻው “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል”የሚለው የክርክር ዘዴ በቁርአን ውስጥ ሳይንስን ሊያገኝ አልቻለም በመሆኑም ከሳይንስ ጥቅምን ከማግኘት ይልቅ ሳይንስ በቁርአን ላይ እንዲፈርድ አድርጎታል፡፡
በsoc.religion.islam የዜና ቡድንና በሌሎችም የቀረበው ሐሳብ ለቁርአን 18.86 በሚሰጠው ትክክለኛ ትርጉምከዚህ በላይ የቀረበው ነጥብ አራት በአስደናቂ ሁኔታ ይረጋግጥልናል፡፡ ያ አረፍተ ነገር አሁንም እዚህ ይገኛል፡-
“ወደ ፀሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት ባጠገቧም ሕዝቦችን አገኘ ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም (በመግደል) ትቀጣለህ ወይም በነርሱ መልካም ነገርን (መማረክን) ትሠራለህ አልነው፡፡” (አማርኛ ትርጉም)፡፡
በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ጥቅሶች ምንም ዓይነት ሳይንስ አላቸው በማለት ማንኛውም ሙስሊም አይናገርም፡፡ ለምን? ምክንያቱም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ያለነው እኛ ሙሉ ለሙሉ ያወቅነው አንድ ሰው በፀሐይ መጥለቂያ ላይ እንደማይደርስ ነው፡፡ እጅግ በጣም ፈጣን የሆነውን አይሮፕላን ተሰጥቶንም እንኳን አንድ ሰው የፀሐይን መጥለቅ ሊከታተልና (ወይንም ሊቀድምም እንኳን) ይችላልና፡፡ በእርግጥም እኛ ፀሐይ በጭቃማ ማጥ ውስጥ፣ በሐይቅ ውስጥ ወይንም በሌላም የውሃ አካል ውስጥ እንደማትኖር እናውቃለን፡፡ ይሁን ደህና መልእክቱ እዚህ ላይ ነው የሚመጣው፡ ሙስሊሞች ይህንን ክርክር ማለትም “ዘመናዊ ሳይንስ በቁርአን ውስጥ ይገኛልን” በመጠቀማቸው ሳይንስ ቁርአንን እንዲፈርድበት አድርገውታል፡፡ እነዚያ ሳይንሳዊ የሚመስሉት ጥቅሶች ተዓምራት ናቸው ተብለው ተጠቅሰዋል (እንደ ተዓምራት ተወስደዋል) እንዲሁም ይህንን የሚቃረኑ ተብለው የተጠቀሱት ጥቅሶች ደግሞ መለኮታዊ እና ምሳሌያዊ ተብለው ተጠቅሰዋል ወይንም ደግሞ ሌላ፡፡ ለምሳሌም፡
ምሳሌያዊ ትርጉም፡-
- ቁርአን 18.86 = የፀሐይን መጥለቂያ ስላገኘ ሰው ይናገራል = ይህ ሳይንሳዊ ትርጉመ ቢስ ነገር ነው = ስለዚህም ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ተብሏል፡፡
ሳይንሳዊ ትርጉም፡-
- ቁርአን 25.53 (ለምሳሌ ያህል) = ስለሁለት የተለያዩ የውሃ አካላት ይናገራል፣ አንዱ ጨዋማ (የማይጠጣ) ሌላው ደግሞ ጨዋማ ያልሆነ (የሚጠጣ) = ይህ ሳይንስን አይቃረንም = ስለዚህም ሳይንሳዊ መገለጥ ተብሎ ተጠቀሰ፡፡
ችግሩን ታያላችሁን? ሙስሊሞች የሚናገሩት ቁርአን የእግዚአብሔር የመጨረሻ መገለጥ ነው በማለት ነው፣ እንዲሁም ቁርአን ለሚኖሩበት መመሪያና (መሪና) በውስጡ ያለው ሁሉም ነገር እውነት ነው በማለት ነው፡፡ ነገር ግን “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለውን ሐሳብ የሚከታተሉቱ የእልምናን መሰረታዊ መርሆ ይቃረናሉ፡፡ ምክንያቱም ሊጂካሊ እንደ መጨረሻ እውነት አድርገው መጥቀስ የሚኖርባቸው ያንን ሳይንስ እንጂ ቁርአንን አይደለም፡፡ ስለዚህም ሳይንስን የሚጠቀሙበት ቁርአንን እንዲበይንላቸው ነው፡፡ (ይህ ደግሞ ለሙስሊሞች ሁሉ አደገኛ አካሄድ ነው፣ ቁርአንን የአምላክ ቃል አድርገው እንዴት ይቀበሉታል?)
ነጥብ አምስት፡ ማንኛውንም ነገር ለማረጋገጥ የተመረጠ አተረጓጎም አገልግሎት ላይ ሊውል ይችላል ማለት ነው፤
ከላይ በነጥብ 4 ላይ እንደገለፅኩት ሁሉ “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለው ሐሳብ የተመሰረተው በተመረጡ አተረጓጎሞች ላይ ብቻ ነው፣ ማለትም ጠቃሚ ናቸው የሚባሉትን ጥቅሶች በማንሳትና በእነርሱ በመጠቀም ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚያን ችግር የሚፈጥሩትን (በመዝጋት) ወይንም በመተው ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ መንገድ አንድ ሰው ማንኛውንም ነገር ለማረጋገጥ ይችላል፡፡ እንበልና እኔ የወደፊቱን ማየት የምችል ነቢይ ነኝ በማለት ሰዎችን ለማሳመን እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህም በእንግሊዝ አገር ውስጥ በእንግሊዝና በስኮትላንድ ቡድኖች መካከል ሕዳር 14 ቀን 1999 ስለሚደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ በቅድሚያ ትንቢትን በወረቀት ጽፌ ነበር፡፡ በጻፍኩትም ትንቢት ላይ የሚከተሉትን ሦስት አረፍተ ነገሮችን አስቀምጫለሁ ይህም ጨዋታው ከመከናወኑ በፊት ነበር፡-
1. ኢንግላንድ ያሸንፋል
2. ስኮትላንድ ያሸንፋል
3. እኩል ለእኩል ይወጣሉ
አሁን ከግጥሚያው በኋላ (እንዳጋጣሚ ኢንግላድ ስኮትላንድን 2 ለ 0 አሸነፈ)፣ ስለዚህም እኔ እንደሚከተለው ተናገርኩኝ፡ “አረፍተ ነገር 2 እና 3 ምሳሌያዊ ናቸው፣ እኔም እነርሱን ቃል በቃል እንዲወሰዱ በፍፁም አላቀድኩም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአንደኛው ተራ ቁጥር ላይ እኔ እውነታን እየተናገርኩኝ ነበር፡፡ ስለዚህም እኔ ነቢይ ነኝ!” በዚህ አቀራረብ ውስጥ ያለውን መሰረታዊ ስህተት ለመረዳት በጣም አዋቂ መሆን አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ይደግፋል” በማለት የሚሰብኩት እነዚያ የሚያቀርቡት ክርክር በትክክል ከዚህ ዓይነት አቀራረብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሳይንስን የሚቃረኑ እጅግ በጣም ብዙ የቁርአንን ጥቅሶች አቅርባችሁ ስታሳዩአቸው (ለምሳሌ ቁርአን 18.86 በተደጋጋሚ ከዚህ በላይ የጠቀስኩትን ዓይነት) እነርሱም የሚናገሩት ነገር “እርሱ ልብ ወለድ ነው ታሪክ ነው” ወይንም ደግሞ “ምሳሌያዊ ነው” ወይንም ሌሎች ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ (ምናልባቶችን ሁሉ) ይነግሯችኋል፡፡ ነገር ግን ወደ እውነተኛ ትንተና ላይ ሲመጣ ግን የነገሩ ፍፃሜ ቃሉ የተነገረበትን ነገር በጭራሽ አያረጋግጥም፡፡
ነጥብ ስድስት፡ ሐሳቡን መጠቀም ማለት ቁርአን ከአሁን በኋላ ምንም ስልጣን ያለው መጽሐፍ አይደለም ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ሙስሊሞች “ቁርአን ዘመናዊ ሳይንስ” አለበት ስለዚህም ተዓምር ነው በማለት ለመናገር ቢሞክሩ፣ በቀጥታ የሚሆነው ነገር ቀጣይ የሆነ ሌላ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ የእነርሱም የመነጋገሪያ ሎጂካዊ ይዘት ሊሆን የሚችለው ቁርአን ከዚህ በኋላ ስልጣን ያለው መጽሐፍ አይደለም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል እንደገና ቁርአን 25.53 እንውሰድ እርሱም “ስለ ባህር ሳይንስ” ያወራል እንበል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ አንድ አረፍተ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ርዕስ ወይንም (ጉዳይ) በተመለከተ ብዙ ለማወቅ ከፈለግን እኛ በቀጥታ መሄድ የሚገባን ከቁርአን ውጭ ነው ምክንያቱም ቁርአን በዚህ ጉዳይ ላይ ስልጣን ያለው አይደለምና፡፡ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ጽሑፎች፤ መጽሐፍት እንዲሁም ሳይንሳዊ ወረቀቶች ስላሉ ቁርአን ከሚለው በላይ በእነርሱ ውስጥ ማንበብ እንችላለን፡፡ በቁርአን ውስጥ ስለተጠቀሰ አንድ ጉዳይን በተመለከተ የውጭ ምንጮችን በማንበብ ብዙ መማር የምንችል ከሆነ፤ የሚከተለው ቁምነገር ወደሚከተለው ጥያቄ ላይ መመራታችን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ጥያቄውም ብዙ የምንማርባቸው ሌሎችስ ጽሑፎች ለሕይወት መመሪያ ለምን አይሆኑም? ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ አንድ ሙስሊም ቁርአን ለሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልገውን መመሪያ ሁሉ የያዘ ነው በማለት እንዴት መናገር ይችላል? ለሕይወት መመሪያ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ምናልባትም እኛ ሌላ ቦታ ሄደን ማንበብ ይኖብናል ማለት ነውን?
ሙስሊሞች ስለ እግዚአብሔር ተፈጥሮ ማወቅ የሚኖርባቸውን ሁሉ ቁርአን ሊያስተምር እንደሚችልስ እንዴት ያውቃሉ? ወይንም አላህ እራሱ እኛ እንዴት መኖር እንደሚገባን እንዴት እንደሚያውቅ በምን ያውቃሉ? ምናልባትም የአጠቃላዩን እይታ ለማግኘት እነርሱ ሌላ ቦታ መመልከት ያስፈልጋቸው ይሆን ይሆናል? ወ.ዘ.ተ፣ የሚሉ ጥያቄዎችን ሁሉ ያስነሳብናል፡፡ ስለዚህም “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለው ሐሳብና ዘመናዊ የመከራከሪያ ዘዴ የቁርአንን ስልጣን ሙሉ ለሙሉ አፈራርሶታል፡፡
መደምደሚያ፡
በተናጠል በተያዘ አንድ ነጥብን ብቻ ይዞ ለመከራከር በጣም የማይቻል ነገር ነው፡፡ ለመስበክ የያዝነውና የምንመርጠው ነገር ሁልጊዜ የሚያስከትላቸው ውጤቶችና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ይህ ሐሳብ “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” ለሚለው አዲስ የመከራከሪያ መንገድ ላይ እውነት ሆኗል፡፡ “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለው ነገር በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ለብዙ ሙስሊሞች በጣም ጥሩና ጥርት ያለ ነገር መስሏል፡፡ በእርግጥ እውነት ቢሆን ኖሮ የቁርአን ማስረጃ ይሆን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን አዲስ ዓይነት መከራከሪያ መንገድ ለመረጠው ሙስሊም ሎጂካዊ ውጤቶቹ አስከፊዎች ናቸው፡፡ እርሱም በጣም የማያነቃንቅ፣ እንዲሁም አላህን ዝቅ የሚያደርግና በዚህ አላህን ዝቅ በማድረጉ ሳያቆም ሳይንስን ከቁርአን በላይ እጅግ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ በስተመጨረሻም የሚያረጋግጠው ምንም ነገር በፍፁም አይኖረውም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቁርአን በማናቸውም ነገር ላይ ያለውን ስልጣን ከምንም ነገር በላይ ያስወግደዋል፡፡ እንደ መከራከሪያም ዘዴ ሲወሰድ እርሱ እጅግ በጣም ደካማና ለሙስሊሞች አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህም እኔ እንደማምነው ሙስሊሞች መልካም የሚሆንላቸው ቢያስወግዱት ብቻ ነው፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-
ከዚህ በላይ ያነበብነውና በአንዲ የተጻፈው ጽሑፍ ሙስሊም ተከራካሪዎች እንዴት በአስጨናቂ ሁኔታ ላይ ያሉ ስለመሆናቸው መሠረታዊ ግንዛቤን ይሰጣል፡፡ “ዘመናዊ ሳይንስ ቁርአንን ያረጋግጣል” የሚለውን መከራከሪያ የሚጠቀሙበት የዜና ማሰራጫ ቡድኖችና ሌሎች ሙስሊሞች የሚያቀርቧቸው ሐሳቦች ሁሉ ከሳይንስ ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው ናቸው፡፡
የአምላክ ቃል ለሳይንስ መኖር ምክንያት ወይንም መሰረት እንጂ ሳይንስ ለአምላክ ቃል መኖር መሰረት ሊሆን አይችልም፡፡ ለማንኛውም ከላይ ባለው ጽሑፍ ውስጥ በስድስት ነጥቦች ዙሪያ የቀረበልን ማስረጃ በየጊዜው በቁርአን ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች ሙስሊሞች በጣም ጋራ ማጋባታቸውን ያሳየናል፡፡
የሕይወት መመሪያ ነው በማለት የምንከተለው ጽሑፍ ወይንም የምናምነው እምነት ጥያቄ ሲፈጥርብን መጠየቅና ትክክለኛም መልስ የማግኘት ሰብዓዊ መብት ሊኖረን ይገባል፡፡ ከቤተሰቦቻችን ወይንም ከአካባቢያችን ስላገኘነው ብቻ የተከተልነው ነገር ሁሉ እውነት ነው በማለት ብቻ የሚፈጠሩብንን ጥያቄዎች ሳናስብባቸው በዝምታ ወይንም በይሉኝታ ታፍነን መኖር አይገባንም፡፡
ብዙዎች ባለማስተዋል ወይንም ባለመጠየቅ ስህተትን እንኳን እያዩ የሚከተሉት እውነት መስሏቸው እንደሚኖሩ የዚህ ገፅ አዘጋጆች ያውቃሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የራሳቸውንና የሌሎችን ጥያቄዎች ለማድበስበስ እንደሚፈልጉና በማድበስበስ ላይ እንዳሉ ወይንም የያዙትን ስህተት ለመልቀቅ እንደማይፍልጉም ይገነዘባሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ያልናቸው የኋለኞቹ ዓይነቶች ግልፅ የሆነውን ስህተት እውነት ለማስመሰል የማይቆፍሩት ጉድጓድ የሌለ መሆኑን ታሪክ ያስረዳናል፡፡
ተሳስተው ለማሳሳት ለሚፈልጉት ሁሉ እውነትና ግልፅ የሆነው ነገር አይዋጥላቸውም፡፡ አንድ ሰው የሚከተለው ነገር እውነት ሆኖ ካላገኘነው የማድበስበሻ ማስረጃ ፍለጋ መሄድ አይኖርበትም፡፡ ይህንን ለማድረግ ማንም አይከለከልም ነገር ግን የዚያ ሰው ሕሊና፣ ማለትም በውስጡ ፈጣሪ ያስቀመጠው ዳኛ አያርፍም ውስጣዊ ሰላምም አይሰጠውም ስለዚህም ከንቱ ድካም ነፋስን እንደመከተል ይሆንበታል፡፡ ትክክለኛውና መደረግ ያለበት ወደ እውነቱ መምጣት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል “እውነት ነፃነትን ይሰጠናል፣ ነፃም ያወጣናል”፡፡
ለሐሰት ማስተባበያን በመፈለግ ጊዜያቸውን ለሚያባክኑና ወደ እውነቱ ሳይመጡ ጊዜያቸውን ለሚያሳልፉ መጽሐፍ ቅዱስ አስገራሚ መልእክት አለው፡፡ ይህም አንደኛው በብሉይ ኪዳን ውስጥ “ቀን የሚያመጣው ምን እንደሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ” የሚልን ሲሆን፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ፣ “የመዳን ቀን አሁን ነው የመዳን ጊዜ አሁን ነው” የሚል እናገኛለን፡፡ መልእክቱም በጣም ሳይዘገይና ጊዜ ሳያልፍብን ወደ እውነቱ አሁኑኑ እንድመጣ ነው፡፡ እስከመቼ በእንደዚህ ዓይነት ሕሊናን በማያሳርፍ አይነት ሕይወት ውስጥ እንቀጥላለን፡፡
ስለዚህም ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን የግል ግንኙነት ላይ ቆም ብለን ልናስብ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ አምላክ ነው፣ እርሱ ሁሉንም ያውቃል በፈቃዱም የሰዎች ልጆች የሚድኑበትን የደኅንነት መንገድ በልጁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት አዘጋጅቷል፡፡
ከእኛ የሚፈለጉ እውነተኛ ነገሮችንም አስቀምጧል እነዚህም እኛ እራሳችን በኃጢአተኝነታችን ምክንያት ከእርሱ መንግስት እና ፍቅር ክልል ውጪ መሆናችንን እንድናውቅና ከእርሱ ጋር የምንታረቅበት ሌላ ሰዋዊና ኃይማኖታዊ እውነተኛ መንገድ በጭራሽ እንደሌለ ነው፡፡
እርሱ ብቻውን የደኅንነትን መንገድ አዘጋጅቶልናል እርሱ ያዘጋጀው መንገድ ደግሞ የዘላለም መንገድ የዘላለም መዳኛ መንገድ ነው የሚገኘውም በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ስራ በማመን ወደ እርሱ መቅረብ ነው፡፡
ደግመን እንለዋለን መንገዱ እራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ቆም በማለት ይህንን መንገድ የምታገኙበትን ሁኔታ እንድትፈልጉ እንመክራችኋለን እግዚአብሔር በምህረቱና በፀጋው ይረዳችሁ ዘንድ ፀሎታችን ነው አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: Can "Modern Science" be found in the Qur’an?
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ